ቀጥታ፡

የተማሪዎች ምገባ መጠነ ማቋረጥን በማስቀረት ውጤት እያስገኘ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረር፤ ጥቅምት 25/2019 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም መጠነ ማቋረጥን በማስቀረት ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ ከተማና ገጠር ትምህርት ቤቶች የ2019 የትምህር ዘመን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት የመደመር መንግስት በትምህርት ጥራት፣ ተሳትፎና የተማሪዎች ውጤት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑት ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተለይም በትምህርት ቤቶች የሚከናወነው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎን በመጨመር እንዲሁም መጠነ ማቋረጥን በማስቀረት ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ የተማሪዎች የትምህርት ቅበላ እንደሚጨምር በማድረግ ረገድ ውጤት እያስገኘ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት ለ2019 የትምህርት ዘመንም ለምገባ ፕሮግራም ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ፕሮግራሙ በማህበራት ለተደራጁ እናቶች የሥራ እድል በመፍጠር የቤተሰብ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ማስቻሉን አመልክተዋል።


 

ፕሮግራሙ በክልሉ መንግሥት በጀትና በማህበረሰብ አቀፍ ተሳትፎ በተጠናከረ መልኩ እየተተገበረ እንደሚገኝ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የፕሮግራሙን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ባለሃብቶች፣ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት የጀመሩትን የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በክልሉ ከተማና ገጠር በሚገኙ 68 ትምህርት ቤቶች ከቅድመ-መደበኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚማሩ 40 ሺህ 672 ተማሪዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም