ቀጥታ፡

በዞኑ ያሉ የልማት ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሮቤ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ያሉ የልማት ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም፣ የሰው ኃይልን በዕውቀትና በሙያ በማብቃትና ምርታማነትን በማሳደግ በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ለሚገኙ አመራሮች የራስን አቅም የመጠቀም ዕቅድን ውጤታማ ለማድረግ የተዘጋጀ ስልጠና በባሌ ሮቤ እየተሰጠ ነው።

በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎችና መሠረታዊ መርሆዎች በተመለከተ በሚሰጠው ስልጠና የክልል፣ የዞኖች፣ ከተሞችና ወረዳዎች የመንግሥትና የፓርቲ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።


 

ስልጠናው የአመራሩን ግንዛቤ በማጠናከር ዕቅዱን በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ወደ ተግባራዊ ሥራ ለመቀየር በቂ ዝግጅት ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

ስልጠናው የመደመር መንግሥትን ራዕይ ወደ ተግባር በመቀየር፣ የሀገር ውስጥ ሀብቶችን፣ የጋራ አቅምንና ያሉትን የልማት ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም በኢኮኖሚ ራስን መቻልን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ኢድሪስ ፤ ዕቅዱን ለማሳካት አመራሮች በውጤት ላይ የተመሠረተ ዕቅድ በማዘጋጀት የታቀዱ ሥራዎችን በጊዜና በጥራት መፈጸም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

እንዲሁም የጋራ ግንዛቤን፣ የሥራ ቅንጅትን፣ የሕዝብ ተሳትፎንና ተጠያቂነትን ማጠናከር የዕቅዱን ግብ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በዞኑ ያሉትን የልማት ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም፣ የሰው ኃይልን በዕውቀትና በሙያ ማብቃት፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ማስፋፋትና ተጠያቂነት ያለውን አሠራር መዘርጋት ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ተመላክቷል።


 

በስልጠናው በዞኑ ራስን የመቻል አቅም የመጠቀም ዕቅድ፣ እንዲሁም በዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተሞች ዕቅድ ላይ ውይይት ይካሄዳል።

ከስልጠናው በኋላ ተሳታፊዎች ያገኙትን ግንዛቤ በዕለት ተዕለት ሥራቸው በመተግበር ዕቅዱ በማኅበረሰብና በቤተሰብ ደረጃ ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል።

በሮቤ ክላስተር እየተሰጠ በሚገኘው የአመራር ሥልጠና ላይ ከክልሉ፣ ከዞኑና ወረዳዎች የተውጣጡ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም