ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉዳያችንን በደቂቃዎች ውስጥ ለማስፈጸም አስችሎናል-ተገልጋዮች 

ደሴ ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በምልልስ በርካታ ቀናትን ይፈጅ የነበረውን ጉዳይ በደቂቃዎች ውስጥ ለማሳካት አስችሎናል ሲሉ የደሴ ከተማ ተገልጋዮች ገለጹ። 

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በምልልስ በርካታ ቀናትን ይፈጅ የነበረውን ጉዳይ በደቂቃዎች ውስጥ ለማሳካት አስችሎናል ብለዋል።


 

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ሼህ ሙስጠፋ አህመድ፤ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ በመከተሉ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት አስችሏል።

በአንድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶችን ማግኘት በመቻላቸው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና አላስፈላጊ ወጪዎችን በማስቀረት ከብልሹ አሰራር እንደታደጋቸው ተናግረዋል።

ከመኖሪያ ቤት ይዞታ ጋር የተያያዘ አገልግሎት ፈልገው ወደ ማዕከሉ እንደሄዱ የተናገሩት ሼህ ሙስጠፋ፣ ቀደም ሲል ጉዳዩን ለማስፈጸም በርካታ ቀናት ይፈጅ የነበረው አሁን በደቂቃዎች ውስጥ አገልግሎቱን ማግኘታቸውን አስረድተዋል።


 

ወይዘሮ ዘርትሁን አረጋ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም በመመላለስ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሁሉንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።

"በተለይም በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ማግኘታችን በተደጋጋሚ ስናነሳው ለነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር መልስ ከመስጠቱ ባለፈ እንግልትንና ድካምን አስቀርቶልናል" ብለዋል።

"በማዕከሉ ሁሉንም አገልግሎቶች በተደራጀ አግባብ በአንድ ቦታ ማግኘት መቻላችን የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ድካማችንን አስቀርቶልናል" ያሉት ደግሞ ሌላዋ ተገልጋይ ወይዘሮ ማህደር ሰባው ናቸው።


 

የደሴ ከተማ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ናትናኤል ከፍያለው በበኩላቸው፣ በማዕከሉ በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በተሳለጠ መንገድ በመስጠት የህብረተሰቡን እንግልትና ድካም ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

አሰራሩ በቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመናዊነትን የተላበሰ በመሆኑ ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ተጠያቂነትም እንዲረጋገጥ አስችሏል ነው ያሉት።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው ፣ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ማሳደግና ብልሹ አሰራርን ማስቀረት ማስቻሉን ገልጸዋል።

አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በሁለት ክፍለ ከተሞች ተጨማሪ ማዕከላትን ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም