የሀገር ውስጥ ምርት አለካክን ቋሚ ዓመት የማድረግ ሥራ ለተሻለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀረጻና የልማት ዕቅድ ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ ምርት አለካክን ቋሚ ዓመት የማድረግ ሥራ ለተሻለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀረጻና የልማት ዕቅድ ያግዛል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አለካክ ቋሚ ዓመት የማድረግ ሥራ ለተሻለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀረጻና የልማት ዕቅድ የሚያግዝ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር የተሻሻለውን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታን ወቅታዊ የማድረግ ስራ ይፋ አድርጎል።
በዚህም የተሻሻለው ጠቅላላ የሀገር ውስጥ መረጃ ቋሚ ዓመት ከ2008 ወደ 2017 ዓ.ም እንዲቀየር ተደርጓል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሀጽዮን ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፤ የተሻሻለው የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ስሌት ቋሚ ዓመት ለውጥ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መጠንና መዋቅራዊ ለውጦች በተሻለ ሁኔታ ለማሳየት፣ ለፊስካልና ለገንዘብ ፖሊሲ ቀረጻ፣ ለዕዳ ዘላቂነት ግምገማና ለኢኮኖሚ ውሳኔዎች የተሻለ መረጃ ማቅረብ ያስችላል።
የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ስሌት የ2017 በጀት ዓመትን በመውሰድ እንደገና ሲሰላ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መጠን ወደ 24 ነጥብ 03 ትሪሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አመልክተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መጠን 31 ነጥብ 86 ትሪሊዮን ብር አድጓል ብለዋል። የቋሚ ዓመት ለውጡ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ የተፈጠሩ የዲጂታል ፋይናንስ፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ዘመናዊ የግብር ለውጦችና ዕድገቶችን በአግባቡ ለማካተት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የተሻሻለው የኢኮኖሚ ስሌት ከዓለም አቀፉ የ2008 ብሔራዊ አካውንት ሥርዓት መመዘኛዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መረጃ ተአማኒነት እንዲኖረው ያግዛል ብለዋል።
ስራው በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በራስ አቅም መከናወኑ የኢትዮጵያን የስታትስቲክስ ሉዓላዊነት ከማጠናከሩም በላይ ዘላቂ ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
አዲሱ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መረጃ በመንግሥት ተቋማት፣ በክልሎች፣ በልማት አጋሮችና በግሉ ዘርፍ በዕቅድ፣ በበጀት፣ በኢንቨስትመንትና በፖሊሲ ውሳኔዎች ላይ በአግባቡ እንዲውል ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ የኢኮኖሚ መረጃ የሀገሪቱን የእዳና የታክስ ምጣኔዎች በተሻለ መልኩ ለመገምገም፣ የታክስ መሠረትን ለማስፋትና የሀገር ውስጥ ገቢ የማሰባሰብ አቅምን ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።