ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ለማስተናገድ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ነብዩ ስሑል ገለጹ። 

ጉባዔው "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ ጥቅምት 26  ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሶስት ቀናት በዓድዋ ድል መታሰቢያ እንደሚካሄድም ተገልጿል።

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ነብዩ ስሑል ጉባዔውን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ ጉባዔው የብልፅግና ፓርቲና የአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል በትብብር ያዘጋጁት ነው።

ጉባዔው ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በአንድ ላይ የሚያሰባስብና ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚወያዩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት ይሆናል ብለዋል።

በጉባዔው እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ አንስተው፤ የሀገራትና የመንግስታት መሪዎች፣ ከፍተኛ የምክር ቤት አባላት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቃነ መናብርት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ኢኮኖሚስቶች፣ ሲቪል ማህበራት እንደሚሳተፉበት ተናግረዋል።

ጉባዔው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድርና ድምፅ ከመሰብሰብ ባለፈ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ያመላክታል ብለዋል።

ፓርቲዎች የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት በማምጣት ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለባቸውም ይመከርበታል ብለዋል።

በጉባዔው የመጀመሪያ ቀን የአፍሪካ ሴቶች የፖለቲካ አመራርና የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ፎረም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በሁለተኛው ቀን የመክፈቻ መርሃ ግብር እንደሚኖርና የሀገራት መሪዎች እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ የተለያዩ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙም ተናግረዋል።

ጉባዔው በተለያዩ ቋንቋዎች የሚመራ እንደሚሆን ጠቁመው፤ ሁሉም ሰው በቂ መረጃ እንዲኖረው ይደረጋልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል መሆኗን ጠቅሰው፤ ለአፍሪካ ነፃነት ትልቅ ሚና ያበረከተች ታሪካዊ ውርስ ያላት መሆኗ ጉባዔውን ለማስተናገድ እንድትመረጥ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት እያከናወነች ያለው ሁለንተናዊ ልማትና የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን እየሰራች በመገኘቷ ጉባዔውን ለማስተናገድ እንድትመረጥ አድርጓታልም ብለዋል።

ፖለቲካ ፓርቲዎች የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መሪዎች እንዲሆኑ ማስቻል የጉባዔው ዓላማ መሆኑንም ተናግረዋል።

በጉባዔው መጨረሻ የአዲስ አበባ የአቋም መግለጫ እንደሚዘጋጅና እነኚህን ጉዳዮች ወደ ተግባር ለመቀየር የተለያዩ ኮሚቴዎች እንደሚቋቋሙም ገልጸዋል።

ጉባዔውን ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁንም አረጋግጠዋል፡፡

የመጀመሪያው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ባለፈው ዓመት በጋና አክራ መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም