በሸገር ከተማ የተለያዩ የግብርና ልማት ኢኒሸቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ የተለያዩ የግብርና ልማት ኢኒሸቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው
ሸገር ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ የተለያዩ የግብርና ልማት ኢንሸቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፤ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ዘመናዊ አገልግሎትን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ኢንሸቲቮች ተነድፈው ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በተለይም የግብርና፣ የትምህርት፣ የጤና እና የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም በከተማዋ የህዝብን የልማት ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ በሂደት ምላሽ የመስጠትና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርትን በብዛትና በስፋት ማምረት አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው፤ በተለይም ለስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የስንዴ ልማትን በመደበኛ ወቅቶች እና በበጋ የመስኖ ልማት ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን የመቻል ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም ከተሞችን ለኢንዱስትሪ ምርት ብቻ ማዋል የሚለውን አመለካከት በመቀየር የግብርና ልማትም የምግብ ዋስትና መሰረት እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማ ግብርና የመሬትና የውኃ አስተዳደር የሚፈልግ በመሆኑ ለአርሶ አደሮች በቂ ሥልጠና በመስጠት በልማቱ ስኬታማ እንዲሆኑ መደረጉንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ኢንሸቲቮች ተነድፈው ወደ ስራ በመግባት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።