የሀገር ውስጥ ምርት አለካክን ወቅታዊ ማድረግ ወደ ተጨባጭ ለውጥና ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያሸጋግር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ ምርት አለካክን ወቅታዊ ማድረግ ወደ ተጨባጭ ለውጥና ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያሸጋግር ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦የሀገር ውስጥ ምርት አለካክን ወቅታዊ የማድረግ ስራ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም በማሰባሰብ ወደ ተጨባጭ ለውጥና ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያሸጋግር መሆኑን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሀጽዮን ገለጹ።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር የተሻሻለውን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታን ወቅታዊ የማድረግ ስራ ይፋ አድርጓል።
በዚህም የተሻሻለው ጠቅላላ የሀገር ውስጥ መረጃ ቋሚ ዓመት ከ2008 ወደ 2017 ዓ.ም እንዲቀየር ተደርጓል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሀጽዮን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ዜጎች በክብር የሚኖሩባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የሀገር ውስጥ ምርት አለካክን ወቅታዊ የማድረግ ስራ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም በማሰባሰብ ወደ ተጨባጭ ለውጥና ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እስከ 2050 የምትመራበት የመደመር መንግሥት ስትራቴጂ ኢኮኖሚውን በመሰረታዊነት የሚቀይር መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ስሌት መሰረታዊ የቋሚ ዓመት ለውጥ ወደ ትክክለኛ ግመታ ያደርሳል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት በግብርና በኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች አዎንታዊ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በሀገራችን የተመዘገቡ ዘርፈ ብዙ ለውጦች በኢኮኖሚ አለካክ ስርዓቱ ላይ ክፍተት ፈጥሮ ነበር ብለዋል።
ስለሆነም በ2017 ዓ.ም ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ አንፃራዊ የዋጋ ግሽበትና የተሻለ የመረጃ ምንጭ፣ የተሻለ የቤተሰብ ጥናት በመገኘቱ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መለኪያ ቋሚ ዓመት እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።
ከመስከረም 2018 እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም ባለው አንድ ዓመት በተደረገ ስራ እንዲቀየር መደረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መለኪያ ቋሚ ዓመት ለመቀየር ዘጠኝ ዓመት የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ በየአምስት ዓመቱ መቀየር የተሻለ እንደሆነ አንስተዋል።
የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ቋሚ ዓመት ለውጥ ወቅታዊ ግምት መሰረት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቱ 59 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።