ቀጥታ፡

በማዕከሉ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እያገኘን ነው- ተገልጋዮች

ሐረር ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተገልጋዮች ገለጹ።

በሐረሪ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ተጠቃሚ አቶ በላቸው ምትኩ ፤ ከዚህ ቀደም አገልግሎቶች የተለያየ ቦታ ተበታትነው ይሰጡ ስለነበር  ለእንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

አሁን ላይ በመሶብ አንድ ማዕከል የተለያዩ አገልግሎቶች በአንድ ቦታና በቴክኖሎጂ ተደግፈው በመሰጠታቸው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ልናገኝ ችለናል ሲሉ  ተናግረዋል።



 

መንግስት መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በማዘጋጀት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ዘርአዳም ዳኛቸው ናቸው።

በማእከሉ የተለያዩ  አገልግሎቶችን በአንድ ቦታና በዲጂታል በመታገዝ በማግኘታችን ጊዜና ወጪን ቆጥቦልናል ብለዋል።

በማእከሉ የንግድ ፍቃድ እድሳትና ሌሎች አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የመሶብ አንድ ማዕከል ጥራትና ተደራሽነትን ያሰፋ የተገልጋዮችን እርካታ ያሻሻለ፣ብልሹ አሰራርን የቀረፈ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሐረሪ መሶብ አንድ ማዕከል የዩኒቨርሳል ባለሙያ ደሴ አህመድ ናቸው።

ማእከሉ ስራ በጀመረበት  በአንድ ዓመት ከአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የዜጎችን እንግልት በማስቀረት ግልጽ፣ ፍትሃዊና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን  ተናግረዋል።



 

የሐረሪ መሶብ አንድ ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብዱልሃፊዝ አህመድ እንዳሉት፣ በማዕከሉ በ10 የክልልና ፌዴራል ተቋማት 113 አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው።

በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሚሰጡ አገልግሎቶች ዜጎች ቀደም ሲል  የሚያነሷቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችንና አቤቱታዎችን በመቅረፍ   ፈጣንና  ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ሶስት ተጨማሪ ተቋማትን ወደ ማዕከሉ በማስገባት አገልግሎቶችን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም