ኢትዮጵያ 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች
ከጥቅምት 26/2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ በርካታ የአህጉሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችን በማሰባሰብ በፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ የሚካሄደው ጉባኤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ከፍ አድርጎ ያሳያል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ገዥና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጠበቀ የፓርቲ ለፓርቲ እና የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት እንድትፈጥር፣ ሀገራዊ እውነታዎቿን እና የልማት ስራዎቿን በቀጥታ እንድታስረዳ ትልቅ እድልም ይፈጥራል።
በቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ፣ የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም እና የአህጉሪቱን ጂኦ-ፖለቲካዊ ነፃነት ለማረጋገጥ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እንዲቆሙ መድረኩ መንገድ ይጠርጋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ እና አካባቢው፣ ኢትዮጵያ የነቃ የሰላም እና የልማት አጋር መሆኗን በተግባር በማሳየት ረገድም ጉባኤው የላቀ ድርሻ አለው፡፡
የፖለቲካ ውይይቱ ከአህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ጋር በመቃኘት፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ማዕከል እንድትሆን የሚደረገውን ጥረትም ያፋጥናል፡፡
የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ አበባ ላይ መምከራቸው፣ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ያላትን መሪነት፣ ተሰሚነት እና ዲፕሎማሲያዊ አቅም በግልጽ የሚያሳይ ተጨባጭ እርምጃ ነው።