በኮፕ 32 ዋዜማ፡ የኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስደማሚ ስኬት - ኢዜአ አማርኛ
በኮፕ 32 ዋዜማ፡ የኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስደማሚ ስኬት
በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዕድገትና ተፎካካሪነት ሲነሳ የብዙዎች አእምሮ የሚያስበው እንደ ኖርዌይ፣ ቻይና ወይም ካሊፎርኒያ ያሉ የበለጸጉ ሀገራትና ከተሞችን ነው።
ነገር ግን፣ ብሉምበርግ “The World's Most Aggressive EV Push Isn't in China” በሚል ርዕስ በሰራው ፕሮግራም ላይ ከማንም በፈጠነ እርምጃና ደፋር ውሳኔ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተሸጋገረችው በመኪና አምራችነቷ የማትታወቀው ኢትዮጵያ መሆኗን ገልጿል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024 የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ ዓለምን ያስደመመ ታሪካዊና ወሳኝ እርምጃ ወስዳለች።
በርካታ የበለጸጉ ሀገራት የነዳጅ መኪኖችን አጠቃቀም ለመቀነስ የአስር ዓመት እቅድ እያወጡ ውሳኔያቸውን በተደጋጋሚ ሲያራዝሙ፣ ኢትዮጵያ ግን እቅዷን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ቀይራለች።
ቀደም ሲል ሀገር ውስጥ ያሉ የነዳጅ መኪኖች መስራታቸውን እንዲቀጥሉ ቢፈቀድላቸውም፣ ከአዲሱ ህግ በኋላ የሚገቡት ግን ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሪክ ብቻ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ይህ ውሳኔ ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዥ ታወጣው የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለመቆጠብ የሚያስችል ትልቅ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ መሆኑ ተጠቅሷል።
በውጤቱም፣ ከህግ ትግበራው በፊት ከነበረው አነስተኛ የኤሌክትሪክ መኪና አጠቃቀም በመነሳት፣ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ ያላቸው ድርሻ ስድስት በመቶ ደርሷል፤ ይህም ከዓለም አቀፉ አማካይ አራት በመቶ በላይ በመሆኑ ሀገሪቱ በቀዳሚ ደረጃ ያስቀምጣታል።
የዚህ ፈጣን አብዮት ሌላኛው ማረጋገጫ በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ የሚታዩ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2022 ከነበረበት 7,000 ተነስቶ በ2025 ከ100,000 በላይ መድረሱ ነው።
ብሉምበርግ በዘገባው እንደጠቀሰው፣ እ.ኤ.አ. በ2024 በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተመዘገቡት መኪኖች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ናቸው።
ይህ ሽግግር የሕዝብ ትራንስፖርትና የታክሲ አሽከርካሪዎችን የኢኮኖሚ አቅም ከመደገፉም በላይ፣ ቀደም ሲል ለነዳጅ ያወጡ የነበረውን ወጪ በመቀነስ በወር እስከ 150 ዶላር እንዲቆጥቡ አድርጓቸዋል፤ ይህም ከጠቅላላ ወርሃዊ ገቢያቸው አንጻር ትልቅ እፎይታ መሆኑ አንስቷል።
ለዚህ አመርቂ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር ስኬት ዋናው መሠረት ሀገሪቱ ያላት የታዳሽ ኃይል አቅም መሆኑንም የብሉምበርግ (Bloomberg) መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት ከሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል 99 በመቶ የሚሆነው ከንጹህ እና ታዳሽ ምንጮች የሚመነጭ ሲሆን፣ 96 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከውሃ ኃይል የሚገኝ ነው።
በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዚህ የትራንስፖርት አብዮት አስተማማኝና ርካሽ የኃይል ምንጭ ሆኗል።
ይህም ሀገሪቱ የራሷን ፍጆታ አሟልታ እንደ ታንዛኒያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ላሉ የጎረቤት ሀገራት ጭምር ኤሌክትሪክ እንድትልክ አግዟታል።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ዋጋ በኪሎዋት ሰዓት 10 ሳንቲም (በአሜሪካ 18 ሳንቲም፣ በእንግሊዝ 40 ሳንቲም መሆኑ ሲታሰብ) እጅግ አነስተኛ ከሚባሉት ተመኖች አንዱ በመሆኑ፣ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ መሙላት አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅና አትራፊ ያደርገዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎችን ከመግዛት ባሻገር የሀገር ውስጥ የመገጣጠም አቅሟ እያደገ እንደሚገኝም እንዲሁ።
መንግሥት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት ባወጣው መመሪያ መሠረት፤ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ 15 በመቶ ቀረጥ የሚጣል ሲሆን፣ በከፊል የተበተኑ (SKD) ክፍሎች ላይ 5 በመቶ ቀረጥ ይከፈላል፤ ሙሉ በሙሉ በነጠላ ክፍሎች (CKD) መጥተው በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙት ግን ምንም ዓይነት ቀረጥ ሳይጣልባቸው እንዲገቡ ይደረጋል።
በዚህም ምክንያት እንደ በላይነህ ክንዴ ያሉ ሀገር በቀል ኩባንያዎች ሚኒባሶችንና የሕዝብ ማጓጓዣዎችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም ጀምረዋል።
የብሉምበርግ ቡድን በበላይነህ ክንድ የማምረቻ ስፍራ በመገኘት፣ በስልጠና ሂደት መጀመሪያ ላይ ከቻይና ኢንጂነሮች ጋር አብረው ይሰሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ባለሙያዎችና ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ሙሉ ስልጠና አግኝተው የምርት ሂደቱን በሙሉ አቅምና እውቀት በራሳቸው እየመሩት እንደሚገኝ ለመመልከት መቻሉን ገልጿል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2033 በሀገሪቱ ያሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ወደ 500,000 ለማድረስና የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ከ2000 በላይ ለማድረስ አቅዳ በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች።
በአሁኑ ወቅትም የኃይል መሙያ መሠረተ ልማቱ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ አልፎ ወደ አዳማ እና ሀዋሳ ባሉ ከተሞች በፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል።
እ.አ.አ በ2027 ኢትዮጵያ 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ታስተናግዳለች።
ጉባኤውን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በራሳቸው አቅም ወደ አረንጓዴና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓት እንዴት በፍጥነት መሸጋገር እንደሚችሉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታሳይበት ታላቅ አጋጣሚ መሆኑን ብሉምበርግ በዘገባው አስታውቋል።