ቀጥታ፡

የማሪን ኮማንዶና ባህረኞች በህዳሴው ግድብ ሀይቅ ላይ የሚያደርጉት የንጋት ቅኝት

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ባሕረኞች ሙያዊ አቅምን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሥልጠና እና የዝግጁነት ተግባራትን ከማከናወን በተጨማሪ በወንዞች ላይ የሚደርስን የደኅንነት ስጋት ለመከላከል አሰሳ እና ቅኝት ያካሂዳሉ።

ኢትዮጵያ የባዕዳንን ከንቱ ቅዥት ሰብራ በዜጎቿ የተባበረ ክንድ በመገደብ የጠላቶቿን አፍ ያዘጋጀችበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚገኙት የባሕር ኃይል አባላት በሐይቅ ላይ የንጋት አሰሳ እና ቅኝት በማድረግ የሐይቁን ዙሪያ ደኅንነት በማረጋገጥ ሕዳሴ ግድቡን ከአደጋ ይከላከላሉ። ይህ የተለመደ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው።


 

በዚህ አሰሳ እና ቅኝት በሐይቁ ወደሚገኙ ደሴቶች እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ፈጣን የጀልባ እንቅስቃሴ በማድረግ ያላቸውን አቅምና ቁርጠኝነት እያረጋገጡ፣ የሕዳሴውን ሰላም አስተማማኝ የማድረግ ተግባራቸው ከሌሎች የሠራዊት ክፍሎች እና የፀጥታ አካላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ እያስጠበቁም ይገኛሉ።

ሀገራችን ያጣችውን የባሕር በር ለማግኘት አሁን ላይ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እየሠራች ባለበት ታሪካዊ ወቅት ባሕር ኃይሏም የተቀናጀ የባሕር ደኅንነት ሥራዎችን በማከናወን እና ሙያተኞችን አቅም በማሳደግ ዝግጁነቱን በማረጋገጥ ላይ መሆኑን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የቀጣናውን ሰላም በማረጋገጥ አይተኬ ተግባር ከመፈጸሙ ባሻገር ቦንድ በመግዛትና ቀጥተኛ የልማት ተሳታፊ በመሆን አጋርነቱን ያረጋገጠ የሰላም እና የልማት ኃይል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም