የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናን ትግበራ ለመደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናን ትግበራ ለመደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናን ትግበራ ለመደገፍና የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ማዕከልን ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ከሁለት ተቋማት ጋር ተፈራረመ።
ሚኒስቴሩ ስምምነቱን የተፈራረመው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ኤክስፐርታይዝ ፍራንስ ከተሰኘ የልማት ድርጅት ጋር ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሃብረቢ ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከኤክስፐርታይዝ ፍራንስ ጋር የተደረገው ሥምምነት የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማሳለጥ ያለመ ነው ብለዋል።
የልማት ድርጅቱ ለትግበራው ውጤታማነት በአውሮፓ ህብረት በኩል የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የነጻ አህጉራዊ የንግድ ትግበራውን የሚያሳልጥ ብሄራዊ ስትራቴጂ አዘጋጅታ ወደ ግብይት ገብታለች ያሉት ሚኒስትር ያስሚን፤ ትግበራውን ውጤታማ ለማድረግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር አጀንዳችን በጠንካራ ተቋማት እና በሰለጠነ የሰው ኃይል ሊደገፍ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ከኤክስፐርታይዝ ፍራንስ ጋር የተፈረመው ስምምነት መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት የኢትዮጵያን የትግበራ አቅም ያሳድጋል ብለዋል።
በኢኮኖሚው ውስጥ የእሴት ሰንሰለት እድገትን ያፋጥናል እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት እና ወጪ ንግድን ለማሳደግ ይረዳል ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን አስታውሰው፤ ስምምነቱ ይሄ ውጥን እንዲሳካም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ሙሉ የንግድ ትስስር ጥቅሞችን ለማግኘት ጥራት ያላቸው ፖሊሲዎችን የማውጣት፣ በምርምርና መረጃ ላይ የተመሠረቱ የንግድ ድርድሮችን የማካሄድ፣ የድንበር አስተዳደርን ውጤታማ ማድረግ እና ጠንካራ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ውይይትን የማጎልበት አቅምን ይጠይቃል ሲሉም ተናግረዋል።
ከኤክስፐርቲዝ ፍራንስ የምናገኘው ድጋፍ በትክክል እነዚህን መሠረቶች እንድንገነባ ይረዳናል ብለዋል።
ሌላው ስምምነት የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር ማቋቋምን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትር ያስሚን ገለጻ፤ የማዕከሉ መቋቋም ለተወሰነ የሙያ ዘርፍ የሚያስፈልግ የሰው ኃይል ልማት እና የፖሊሲ ምርምር ጠንካራ መሠረት ይጥላል።
ማዕከሉ አዳዲስ የንግድ ተደራዳሪዎችን እና የፖሊሲ ተንታኞችን የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ በቀጣናዊ ትስስርና ልማት ዙሪያ ልዩ የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ይጀምራል።
እንዲሁም ሀገራዊ የንግድ ስትራቴጂዮችን በቀጥታ የሚደግፉ መደበኛ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ፖሊሲ ውይይቶችን ያመቻቻል፤ በተጨማሪም ጽኑ የቀጣናዊ እሴት ሰንሰለቶችን እንድንገነባ ያስችለናል ሲሉም አብራርተዋል።
የምናቋቁመው ማዕከል ለመላው አህጉር የእውቀት፣ የምርምር እና የክህሎት ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው ያሉ ሲሆን፤ በሙሉ አፍሪካ ነጻ ንግድ ትግበራን የሚደግፍ እና በአጀንዳ 2063 ስር ያሉትን የጋራ ምኞቶቻችንን የሚያስቀጥል ይሆናል ብለዋል።
የኤክስፐርታይዝ ፍራንስ የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዣን-ባፕቲስት ፔቲኚ በበኩላቸው፤ የልማት ድርጅቱ የመንግሥት ተቋማትን አቅም ማሳደግ፣ አነስተኛና መከካለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲጠናከሩ እና ወደ አፍሪካ ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የተቋማት ቅንጅት እንዲሳለጥ መደገፍ በኛ በኩል የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የእውቀት ሽግግሩን መደገፍ፣ ባለሙያዎችን ማምጣትና እንዲያሰለጥኑ በማድረግ ዘላቂ ብሄራዊ የአቅም ግንባታዎች ላይ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ትግበራ የጎላ ሚና እንዲኖራት ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር እና በአቅም ግንባታ ረገድ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።