ቀጥታ፡

የናይጄሪያው ልኡክ አባል ስለአዲስ አበባ ምን አለ?

ከሳምንት በፊት በናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሸቲማ ከሚመራው ከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ልኡካን ጋር አዲስ አበባ እንደነበረ ይናገራል። እንደ በርካታዎቹ የሃገሩ ዜጎች የአዲስ አበባ ቤተኛም እንደሆነ አንስቷል። የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ጉዞው ግን ከዛሬ አስር ዓመት በፊት እንደነበረም አስታውሷል። ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያንም በደንብ አድርጎ እንደሚያውቀው ጠቅሷል።

ከሀገራሩ ከፍተኛ የመንግስት ልኡካን ጋር የመጣው የኢትዮጵያና የናይጄሪያ የስነ ምግብ አመራር (Nigeria-Ethiopia Nutrition Leadership Exchange) ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሆነ ያነሳው ይህ ልኡክ በውስጡ ደጋግሞ የሚያነሳው ኢትዮጵያ እራሷን መመገብ ከቻለች እኛ ናይጄሪያምያን ታዲያ ምን ሆነናል? ለዚህ የሚሆን ምንም ሰበብ የለንም? በማለት የሃገሩን ነባራዊ ሁኔታ ያነጻጽራል።

በህዝብ ቁጥር ብዛት ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥላ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም በግብርና ምርት ላይ ያሳየችው እመርታ ተአምር ሆኖበታል ለዚህ ናይጄሪያዊ ጆናታን ኢሳያህ ። ይሄንንና ሌሎች ሃገራዊ ንጽጽሮችን እያሰበ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሲዘዋወር ነው እንግዲህ ሌላውን ነገር የታዘበው።

በናይጄሪያው ታዋቂ ጋዜጣ ሊደርሺፕ/LEADERSHIP/ ኤዲቶሪያል ቦርድ አባልና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው ይህ ሰው አዲስ አበባ የመጣው ለጉብኝት እንዳልሆነ ቢናገርም የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ ጉዳይ እንዴት ቢሰራ ነው የሚለውን ሃሳቡን እያወጣና እያወረደ በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ያደረጋቸው ጉዞዎች ናቸው ተጨማሪ ግርምትን የጫሩበትና ይሄንኑ ሃሳቡን በዚሁ ጋዜጣ ላይ በምስል አስደግፎ ዘለግ ባለ ጽሁፍ እንዲያወጣው ያደረገው።


 

ከአዲስ አበባ ቆይታዬን ጨርሼ የወጣሁት በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው ይላል። ባየሁት ነገርና ኢትዮጵያውያን ባስመዘገቡት ስኬት ሁሉ ተገርሜያለሁ ያለው ኢሳያህ የሃገሩ ከፍተኛ የመንግስት ልኡካንም በጣም እንዳደነቁት ተናግሯል። የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሸቲማን ጨምሮ የሀገሪቱ መንግስት ከፍተኛ ልኡካንም በኢትዮጵያውያን ስኬት የተደመሙት የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ባደረገችው ጥረትና ባስመዘገበችው ስኬት ብቻ ሳይሆን በከተማዋ በተስተዋለው ፈጣንና አስደናቂ ስኬትም ጭምር እንደነበረ ያወሳል።

ሆኖም በጣም አዝኛለሁ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ያላት ሁሉ እኛም አለን ፤ ብዙ ገንዘብ ፣ብዙ ህዝብ፣ እና ሌሎችም ነገሮች አሉን እኛ ያጣነው ነገር ቢኖር አንድን ነገር ጀምሮ እስከ መጨረሻው ማከናወንና ውጤቱን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገው ቁርጠኝነትና ትዕግስት ነው ብሏል። እንደ ኢትዮጵያውያን መስራት አልቻልንም በመሆኑም አሁን እነሱ ያላቸው ደግሞ እኛ የለንም ይላል ቁጭቱን በገለጹበት የጋዜጣው ትንታኔ ላይ ።

በስራ ዘመኔ በርካታ የአውሮፓ ሃገራትን አይቻለሁ ከተሞቻቸውን ጎብኝቻለሁ አንዳንዶቹ የአዲስ አበባ ከተማ ክፍሎች ከነሱ ጋር የሚወዳደሩ እንደሆኑ ያለምንም ጥርጥር መናገር እችላለሁ ይላል። ንጹህ መንገዶች ዘመናዊ ማሳለጫዎች የከተማው አጠቃላይ ገጽታ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን በፍጹም ተኝተው እንደማያሳልፉ ያሳያሉ ሲልም ገልጿል።

ተንታኙ ከልኡካን ቡድኑ ጋር ከሣምንት በፊት በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ አዲስ አበባን ጨምሮ የመጣበትን የግብርና ምርትና ምርታማነት ውጤታማ ተሞክሮ ለማየት ከአዲስ አበባ በመውጣት ያደረገው የመስክ ምልከታም በዚሁ ጽሁፉ ላይ በስፋት እንዲካተት አድርጓል።

“ሀገራችንን የዘመናዊ ከተሞች ባለቤት የማድረግ ጉዞ በመርህ መመራት አለበት። ነባር ትንንሽ ከተሞችን ማዘመን እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቁ አዳዲስ ከተሞችን መገንባት ያስፈልጋል። በነባር ከተሞቻችን የተዘረጉ ጊዜ ያለፈባቸውም ይሁኑ ያልተዘረጉ የመሰረተ ልማቶች በዘመናዊና የወደፊቱን ታሳቢ ባደረጉ መሠረተ ልማቶች መለወጥ ይኖርባቸዋል” …የመደመር መንግስት መጽሐፍ ገጽ 234

ለውጥን ለማምጣት በቁርጠኛ አመራር እና ውጤትን ቀድሞ ጨርሶ በማለምና ያለዝለት በትጋት በመስራት ግብን ማሳካት እንደሚቻል ጉልህ ማሳያ ከሚሆኑት አስደማሚ የሀገራችን ስኬቶች መካከል በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ታላላቅ ከተሞች የተከናወነው የኮሪደር ልማት ዋቢ ነው። ውጤቱን ማድነቅ አንዳለ ሆኖ በፈተናዎች የማይበገር ጽኑ የመጨረሻ ግቡንም ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ያደረገ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም