ሠራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመፈፀም የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት ላይ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመፈፀም የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት ላይ ይገኛል
ሐረር፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመፈፀም የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት ያለው መሆኑን የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ፍቃዱ ጸጋዬ ተናገሩ።
የምስራቅ ዕዝ መምሪያ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ የተፈፀመበትን ክህደት “እንዳይደገም ሁሌም እንዘክረዋለን” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች አስቦት ውሏል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ ሌሎች የክልሉ አመራሮች፣ የሠራዊቱ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።
የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ፍቃዱ ጸጋዬ፤ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር በሰሜን ዕዝ ላይ በባንዳዎች የተፈፀመው እኩይ ተግባር ሀገር የማፍረስ ዓላማ የነበረው መሆኑን አንስተዋል።
በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ሠራዊቱ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ትልቅ መስዋእትነት የከፈለ መሆኑን አስታውሰው፤ እለቱ ሲታሰብ በሠራዊቱ የተከፈለውን ዋጋ በማስታወስና የካሃዲዎችን እኩይ ተግባር በማውገዝ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ሠራዊቱ የተፈጸመበትን ክህደትና በደል በጽናት በማለፍ የአገር ደህንነትና ዛሬ የህዝብ ሰላም ዘብ በመሆን እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ ተልእኮውን በላቀ ብቃት ለመፈፀም የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት ያለው መሆኑንም ሜጀር ጄነራሉ ተናግረዋል።