ፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ባሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ባሻገር
ፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ባሻገር
በቤተልሔም ባሕሩ (ኢዜአ)
የአንዳንድ አፍሪካ ሀገራት የመንግስታት ምስረታ ከረብሻ፣ መፈንቅለ መንግስት፣ ትጥቅ ትግልና ከውስጥ ከሚነሱ የሴራ ፖለቲካዎች የሚነሳና ለዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ያልታደለ ስለመሆኑ የአደባባይ ሀቅ ሆኖ ቆይቷል። ይህ የፖለቲካ ምህዳር በአህጉሪቷ ላይ የተጋረጠውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ፈተና በሚያሳይበት በዚህ ዘመን፣ ፖለቲካዊ ሰላምንና የተረጋጋ ስርዓትን ማስፈን የዘመኑ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል።
ይህንን አህጉራዊ ፈተና በመስበር ፈር ቀዳጅ ሆና የወጣችው ኢትዮጵያ በቅርቡ ከ50 ሚሊየን ህዝብ በላይ የተሳተፈበትን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማካሄድ ለዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምህዳር ምቹ መደላድል በመፍጠር ለአህጉሪቷ አዲስ ተስፋና አብነት መሆን የቻለ ታሪካዊ ተግባር አከናውናለች።
በህዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤቶች ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወንበር አግኝተው የዲሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ከማድረግ ባሻገር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሴቶችን በማካተትና በማሳተፍ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ያሳየች ተምሳሌት ሀገር ናት። ፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫና ስልጣን ለመያዝ ከሚደረግ ፉክክር ባሻገር ለሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ ለውጥና ዘላቂ እድገት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባና የእውነተኛ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ዋና መሳሪያ መሆናቸውን በተግባር ያሳየው በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግስት ነው።
ባለፉት ስምንት ዓመታት የሀገሪቷን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በመደመር እሳቤ ሀገሪቷን እየመራ ያለው መንግስት፣ ምርጫን ከስልጣን ማግኛ መሳሪያነት ባሻገር የልማት ሞተርና ለህዝብ የተገባ ቃልን በተግባር በመተግበር አስደማሚ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
የመደመር መንግስት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በመዋቅራዊ ለውጦች ሀገሪቷ በግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ በኢንዱስትሪ ልማትና ምርታማነት፣ በቱሪዝም፣ ማዕድንና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ለእድገት መሰረት መጣል ችሏል። በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማጠናከርም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተቀርፆ እየተተገበረ ይገኛል። በዚህም ሀገራችን ከዘመናዊነት ተከታይነት ተላቃ ወደ ቴክኖሎጂ ዓለም መሪነት የሚያደርሷት ተግባራት ተከናውነዋል።
በአሁኑ ወቅት በ78 የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የሀገራችንን ገፅታና የህዝቡን የኑሮ ደረጃ የቀየረ፣ የከተሞችን ትንሳኤ በተግባር ያረጋገጠ ህያው ምስክር ሆኗል። የህብረት ውጤት ማሳያ የኢትዮጵያዊያን የማድረግ አቅም ምልክት የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምረቃ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያበሰሯቸው የጉባ ብስራቶችም ብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግስት ከቃል ባሻገር የሆኑ ተግባራት አብነቶች ናቸው።
በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎች፣ የኒውክለር ኃይል ልማት እንዲሁም የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት መሪው ፓርቲ ከምርጫ ባሻገር ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት እየተጋ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዩኒቨርሲቲ ግንባታም የሀገራችን የነገ ብሩህ ተስፋ በፅኑ መሰረት ላይ እየተገነባ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው ስኬቶች ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን ብሎም እይታዋን እያሳደጉ መጥተዋል። በዚህም በርካታ ኮንፍረንሶችን በማስተናገድ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል የሆነች የዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ሆናለች። ሁለንተናዊ የዲሞክራሲና የልማት ስኬት ተምሳሌትነቷ ማረጋገጫ የሆነ ጉባዔንም ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች። በብልፅግና ፓርቲ መሪነት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ለማስተናገድ እንድትመረጥ አድርጓል።
ጉባዔው ከጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2019ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚህ አህጉራዊ መድረክ ላይ ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ሊቀ መንበሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባዔው "Governing for Growth: Political Parties as Architects of Economic Future" (ለእድገት ማስተዳደር፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች የኢኮኖሚ መፃኢ እድል ቀራፂዎች) በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ ፓርቲዎች ከምርጫና ስልጣን ማግስት ባሻገር ለሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን መሳሪያና ሞተር መሆን እንደሚገባቸው በሰፊው የሚመከርበትና ተሞክሮ የሚቀሰምበት ታሪካዊ መድረክ ይሆናል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ (The First APP Summit) ባለፈው ዓመት በጋና አክራ ከተካሄደ በኋላ ሁለተኛውን ለማስተናገድ አዲስ አበባ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን እየተጠባበቀች ትገኛለች።