ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ 41 ሚሊዮን ዜጎችን የአይን ጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የሁለት ሚሊዮን ዶላር እቅድ ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እስከ  እ.ኤ.አ. እስከ 2030 41 ሚሊዮን ዜጎችን የአይን ጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የሁለት ሚሊዮን ዶላር እቅድ ይፋ አድርጋለች።

 የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የአይን ጤና ጉባኤ በአንቲጓዋ እና ባርቡዳ ሴንት ጆንስ ከተማ ተካሄዷል።




ጉባኤው የተካሄደው በአንቲጉዋ እና ባርቡዳ ፣ በባንግላዲሽ፣ ጉያና፣ አየርላንድ እና ናይጄሪያ መንግስታት አዘጋጅነት፣ በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ጋር እንዲሁም በዓለም አቀፉ የዓይን ዓይነ ስውርነት መከላከል ኤጀንሲ (IAPB)  አስተባባሪነት ነው።

 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2030 ባስቀመጠው ራዕይ መሰረት ሁለንተናዊ የዓይን ጤና እንክብካቤን እውን ለማድረግ ያለመው ይህ ታሪካዊ ጉባኤ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዕይታ ማጣት እና በተለያዩ የአይን ጤና ችግሮች ላይ የሚገኙ ሚሊዮኖችን ከችግር ለመታደግ ትልቅ ምዕራፍ ሆኗል። በዚህ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፎ አድርጋለች።

በጉባኤው ላይ የጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎትና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀገራዊ የህክምና ዘመቻዎች አስተባባሪ እና የሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሌሊሳ አማኑኤል ተገኝተዋል።
 
በዚሁ መድረክ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የአይን ጤና አገልግሎትን ከሀገሪቱ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ጋር በማቀናጀት ላከናወነችው አርዓያነት ያለው ሥራ «Global Vision Impact Award»  የተሰኘ ሽልማት ተበርክቶላታል።

ይህ እውቅና የተሰጠው ሀገሪቱ የመጀመሪያ ደረጃ የአይን እንክብካቤን እና የህብረተሰብ አቀፍ ምርመራዎችን ከብሔራዊ የጤና ስርዓቷ ጋር በማዋሃድ በህዝብ ጤናው ዘርፍ ላመጣችው የላቀ ለውጥና ስኬት መሆኑ በጉባኤው ላይ ተገልጿል።

 በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ማህበረሰብ አቀፍ የዓይን ምርመራ እና የመጀመሪያ ደረጃ የዓይን ህክምና አገልግሎትን በማስፋት፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ ቢያንስ 41 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሁለት ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍና እቅድ ይፋ አድርጓል።

ይህ ኢንቨስትመንት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ3,200 በሚበልጡ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ውስጥ ጥራት ያለው የአይን ህክምናን ለማጠናከር፣ የመነጽር አቅርቦትን ለማስፋፋት፣ የቅድመ-ምርመራ እና የሪፈራል ስርዓትን ለማሻሻል እንዲሁም የዓይን ሞራ ህመም ቀዶ ህክምና ጥራትና ውጤትን ለማሳደግ ያለመ ነው።

ይህም ከእ.አ.አ 2030 በፊት 50 በመቶ የሚሆኑ የትምህርት ቤት ተማሪዎችን የአይን ጤና ሽፋን ስር ለማካተት ለተያዘው ሀገራዊ ግብ ትልቅ ድጋፍ ይሆናል።

የጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎቶችና ፕሮግራሞች ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ሌሊሳ አማኑኤል በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በእድሜ፣ በፆታ፣ በገቢ፣ በዓይን ሞራ ህመም ወይም በመኖሪያ ቦታ ሳይወሰን ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የአይን ህክምና እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በህብረት በመስራት መከላከል የሚቻልን የእይታ ማጣት መቅረፍ እና እይታን መመለስ እንደሚቻል የጠቆሙት ዶ/ር ሌሊሳ፤ ይህም ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤና ስርዓት እውን ለማድረግ እንደሚረዳ አመልክተዋል።
 


 

የ«Cure Blindness Project» ዋና ስራ አስፈፃሚ ኬ-ቲ ኦቨርቤይ እና የዓለም አቀፉ የዓይን ዓይነ ስውርነት መከላከል ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ሆላንድ በበኩላቸው፤ ጉባኤው ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሰበሰበ እና የበርካታ ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት ለመለወጥ የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የዓይን ጤና ስራዎችና የቀዶ ህክምና አገልግሎቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
 
በጉባኤው ላይ ይፋ እንደተደረገው፣ “Vision Action Fund” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ለኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ እና ሱዳንን ጨምሮ ለ24 አገራት የ10 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

 የዚህ ድርጅት ዋና ዓላማም አገራት የአይን ጤና እንክብካቤን ከብሔራዊ የጤና ስርዓታቸው ጋር እንዲያዋህዱ ማገዝ፣ ህብረተሰቡ ጥራት ያለው የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እንዲያገኝ ማድረግ እና የመነጽር አቅርቦትን ማመቻቸት ነው።

 በተጨማሪም እንደ «ኦርቢስ ኢንተርናሽናል» ያሉ ተቋማት ከ2027 እስከ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚውል የ32 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብና ቴክኒካዊ ድጋፍ ይፋ አድርገዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ እ.ኤ.አ. ከ2030 በፊት ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ የተባሉ ከ200 በላይ አዳዲስ ቃልኪዳኖች ተገብተዋል።

በጉባኤው ላይ በቀረበው መረጃ መሰረትም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1.1 ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በቅድመ መከላከል ወይም በሕክምና ሊድኑ የሚችሉ የእይታ ማጣት ችግር እንደሚገጥማቸው እና ከ2 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የተለያዩ የእይታ እክሎች እንዳሉባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም