ኢትዮጵያ እና ቻይና ሁለገብ ወታደራዊ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቻይና ሁለገብ ወታደራዊ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና ሁለገብ ወታደራዊ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ ሁለቱ ሀገራት የቆየና ፍሬያማ የሆነውን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከርና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚሠሩ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሩ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመን የተሻገረና በብዙ መስኮች ፍሬያማ የሆነ አጋርነት እንዳላቸው ጠቁመው፤ በተለይም በወታደራዊ ዘርፍ የቆየውን ጠንካራ ግንኙነት በማስቀጠል፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥልጠና ዕድሎች በኩል ያለውን ትብብር ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ አስምረውበታል።
በተጨማሪም አቶ መሐመድ እድሪስ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር እየሄደችበት ያለው ፍትሐዊ ጥረት ለቀጣናው እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው በማረጋገጥ፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ትብብር የበለጠ ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል።
በተለይም በመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚደረጉ አጋርነቶችንና በኢንቨስትመንት በኩል የተመዘገቡ ፍሬያማ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከምንግዜውም በላይ ቻይና ዝግጁ መሆኗን እንደገለጹ የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።