ለአፍሪካ ዴሞክራሲ መጻኢ ጉዞ በዓድዋ ጥላ ሥር - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ዴሞክራሲ መጻኢ ጉዞ በዓድዋ ጥላ ሥር
አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይልና የብዙ ዕድሎች ባለቤት ስትሆን፣ ይህንን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት ለመቀየር የፖለቲካ አመራርና የኢኮኖሚ ዕድገት ትስስር ወሳኝ ነው። ይህንን አህጉራዊ አጀንዳ የሚያስቀድመው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በሀገራት መሪዎች፣በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ በፖሊሲ አውጪዎችና በተለያዩ ዘርፎች ተወካዮች ጨምሮ በርካታ ተሳታፊዎች በሚታደሙበት በዚህ ታላቅ ጉባኤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአፍሪካ ሁለንተናዊ እድገት ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርጉበት ይጠበቃል።
ይህ ጉባኤ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱ የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት መነሻ፣የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ጽኑ መሠረት እና የአፍሪካውያን የአንድነትና የድል አርማ ከሆነው ታሪካዊ ሁነት ጋር ያገናኘዋል።ዛሬም በዓድዋ ጥላ ሥር አፍሪካውያን መሪዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት ተሰባስበው የአህጉራችንን የዴሞክራሲ መጻኢ ዕጣ ፈንታ መወያየታቸው ያለፉትን አባቶች አርቆ አስተዋይነትና ተጋድሎ የሚዋጅ ታሪካዊ ክስተት ነው።
የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነችው እና በመደመር እሳቤ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት ገጽታዋን በመቀየር አፍሪካን የምታኮራ ተምሳሌታዊ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫና ከሥልጣን ውድድር ባለፈ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ለውጥ የሚመሩ ፖሊሲዎችንና ዘላቂ የልማት ስትራቴጂዎችን ላይ በጋራ ድምጻቸውቅን ያሰማሉ።
በጋና አክራ የተካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ በዴሞክራሲ፣ በአካታች አስተዳደርና ልማትን በሚያስቀድም ፖለቲካ ላይ የጋራ ቁርጠኝነትን ያስቀመጠ ሲሆን፣የአዲስ አበባው ጉባኤ ደግሞ ይህንን ቁርጠኝነት ወደ ተግባራዊ ለውጥ የሚያሸጋግር ነው።ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች ያስመዘገበቻቸውን ስኬታማ ተሞክሮዎች በጉባኤው እንደምታቀርብም ይጠበቃል።
የአፍሪካ የወደፊት ዴሞክራሲ እውን ሊሆን የሚችለው አህጉራችን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታና የባህል እሴቶች ባገናዘበ መልኩ፣ በጋራ በመተሳሰብና በልዩነቶች ውስጥ አንድነትን ማጠናከር ሲቻል ነው።
አሁን ላይ የአፍርካን የኢኮኖሚ ነፃነትን እና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የዓድዋ መንፈስ የቀጣይ ዘመን መገለጫ እንዲሆን ይጠይቃል።በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄደው ይህ ውይይት አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው የሚወስኑበት፣ ጠንካራ ተቋማት የሚገነቡበት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።
ዓድዋ የትናንት የአፍሪካዊያን ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ የነገው የአፍሪካ ዴሞክራሲ እና የነፃነት ብርሃን ማማ ነው።ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤም በዚሁ ታሪካዊ ስፍራ መካሄዱ አህጉራችን በአንድነት፣ በሰላም እና በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ-መንግስት የተገነባ ብሩህ ተስፋ እንዳላት በሰፊው የሚያረጋግጥ ነው።