ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ እድገት እንዲኖረው አስተዋፅኦ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦አገር አቀፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ እድገት እንዲኖረው አስተዋፅኦ ማድረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ባደረገው ስምንተኛ ስብሰባ ውሳኔ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በሩብ ዓመቱ የሸቀጦች የወጪ ንግድ፣ በተለይም የወርቅና የቡና አፈፃፀም ገቢ አዎንታዊ ዕድገት ማሳየቱንና የገቢ ሸቀጦች እድገትም ከፍተኛ ነው። 

አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ ዕድገት እንዲኖረው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።

ማሻሻያው በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ ብሄራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአነስተኛ መስፈርት በእጅጉ የላቀ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አስችሏል ብለዋል።

ከአቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ከፍ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት መቀነስ ያሳየ ቢሆንም በመስከረም 2019 ዓ.ም የታየው 14 ነጥብ 9 በመቶ ግን ከባንኩ የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት ግብ አንጻር ከፍተኛ መሆኑን ኮሚቴው ገምግሟል ብለዋል።

በመስከረም 2019 ለታየው የዋጋ ግሽበት በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትን ተከትሎ የተፈጠረ የአቅርቦት ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ኮሚቴው መገንዘቡን አመልክተዋል።

ኮሚቴው የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠናክሮ እንደቀጠለ መገንዘቡንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች በ2019 በጀት ዓመትም የተጠናከረ እድገት እንደሚኖር እንደሚያመላክቱም ገዥው ተናግረዋል። 

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሲሚንቶ ምርት፣ በኤሌክትሪክ ማመንጫና በብረታ ብረት ነክ ምርቶች ላይ መሻሻል መታየቱን አስረድተዋል።

በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የባንክ ዘርፉ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድርና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል። 

የበጀት ፖሊሲ ስርዓት ጥንቃቄ የተሞላበትና ከብሄራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ከአጠቃላይ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ጋር የተናበበ መሆኑን ኮሚቴው መገንዘቡንም አስረድተዋል።

ፖሊሲው ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲና ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ጋር የተናበበ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ብድር ሳይወስድ ከ27 ወራት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰው፤ ይህም የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም