ቀጥታ፡

በክልሉ ዜጎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ጎንደር ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ በማዘመን ዜጎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የዲጂታል 2030 ስትራቴጂክ ትግበራና አጠቃላይ የዲጂታል አገልግሎትን ማሳለጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጎንደር ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የዴሊቨሪ ዩኒት ሃላፊ አቶ ሞገስ ተኬ፤ የዲጂታል ስትራቴጂክ ትግበራና የአገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም በክልሉ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለ5 ሚሊዮን ዜጎች የዲጅታል ክህሎት ስልጠና ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

​በዚሁ መሰረት በዘንድሮው በጀት ዓመት ሦስት ወራት ብቻ ከ300 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ስልጠናው መሰጠቱን አንስተዋል።

በክልሉ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ በማዘመን ዜጎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የአማራ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ፤ በዚህ ዘመን የዲጂታል መሰረተ ልማት ለኢኮኖሚ እድገት ዋነኛ መሰረት መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በክልሉ የዲጂታል ስትራቴጂክ ትግበራን በማሳለጥ፣ በዘርፉ ብቁ የሰው ሃብት በማፍራትና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም