ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ ነን - የሠራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ ነን - የሠራዊት አባላት
ጅማ ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት መከበርና ለዜጎች ዘላቂ ሰላም የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የሠራዊት አመራሮችና አባላት ገለጹ።
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አመራሮችና አባላት የሰሜን እዝ የተከዳበትንና ግፍ የተሰራበትን ጥቅምት 24 በማሰብ የውይይትና ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮችን አካሂደዋል።
የሰሜን ዕዝ ባልደረባ የነበሩትና አሁን ላይ በዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል ሌቺሳ መገርሳ፣ የጥቅምት 24 በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው ክህደትና ጥቃት የካሃዲዎችና ባንዳዎች እኩይ ተግባር መሆኑን አስታውሰዋል።
በመሆኑም የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲህ አይነቱን አስቸጋሪ ጊዜ በጽናት በማለፍ ሀገሩንና ህዝቡን በላቀ ዝግጁነት በማገልገል ላይ ይገኛል ብለዋል።
የሀገር አለኝታና የሕዝብ መሰረት ያለው ሠራዊት በመሆኑ በህዝቡ ድጋፍ ትብብርና እገዛ ዛሬ ላይ በጠንካራ ቁመና እና የላቀ ዝግጁነት ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የእዙ የሕክምና ዳይሬክተር ኮሎኔል ፍቃዱ ወልደሰንበት፣ ሰራዊቱ በሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በውጊያ አቅም የማይበገር አቅም የገነባ መሆኑን አንስተዋል።
ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት መከበርና ለዜጎች ዘላቂ ሰላም የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የቀድሞ የሰሜን ዕዝ ባልደረቦች የነበሩትና አሁን ላይ የዳሎል እዝ መኮንኖች መቶ አለቃ ዘርትሁን ካሳው እና ሻለቃ ባሻ በሀይሉ፤ መከላከያ ሠራዊት ሀገሩን እና ህዝቡን ለማገልገል በላቀ ዝግጁነት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመው የታሪክ ጠባሳ ሲታወስ ይበልጥ ብርታትና ጥንካሬ የሚሰንቁበትና ለላቀ ሀገራዊ ተልእኮ የሚዘጋጁበት መሆኑን የእዙ አመራሮችና አባላት በመድረኩ ላይ አረጋግጠዋል።