ቀጥታ፡

የመቀሌ እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራ ጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦ የመቀሌ እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራ መጀመራቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።

የአክሱምና የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን እየተቀበሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አዲስና ነባር ተማሪዎቻቸውን በመቀበል የመማር ማስተማር ሥራ ጀምረዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዓብደልቃድር ከድር (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ገቢና ነባር ተማሪዎችን በመቀበል መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በትምህርት ዘመኑ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመቀበል ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ አስረድተዋል።

የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ነጋ ዓፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው አዲስና ነባር ከ1 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን በመቀበል በተያዘው ሳምንት የመማር ማስተማር ሥራ ጀምሯል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ራያ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው እየገቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከጥቅምት 23 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ገቢና ነባር ተማሪዎችን ቅበላ እየተካሄደ ነው ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ ናቸው።

ተማሪዎችንም በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች ደማቅ አቀባበል በማድረግ የተሟላ የመማር ማስተማር ሥራን ለማስጀመር ሙሉ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በዚህም የአክሱም ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ዘመኑ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ አዲስ ገቢና ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ገብረሚካኤል ወልደገብርኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡ 1 ሺህ 500 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ጨምሮ የነባር ቅበላ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር መስተጓጎል ሂደት በመገምገም ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተማሪዎችን በመቀበል መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ እየተገባ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው የሚሰጡትን መመሪያዎችና ደንቦች በአግባቡ በመከተል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ለውጤት እንዲተጉ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም