ቀጥታ፡

በመዲናዋ የተቀናጀ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ የኢትዮጵያን የስፖርት ገጽታ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የተቀናጀ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ የኢትዮጵያን የስፖርት ገጽታ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ እንደሚገኝ የተለያዩ ስፖርት ዘርፍ አመራሮች ገለጹ።

የመደመር መንግሥት በከተሞች ልማት ማዕቀፍ ውስጥ ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ ዘመናዊና አካታች የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የከተሞችን ገጽታ በተጨባጭ እያዘመነ ይገኛል።

በተለይም በአዲስ አበባ የተገነቡት አዳዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ሕፃናትን፣ ወጣቶችን እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችንም ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

እነዚህ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከመደገፍ ባለፈ ጤናማና አምራች ተተኪ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል ዕድል ፈጥረዋል።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ስታዲየሞች መገንባት ለአትሌቶች ውጤታማነት እና ታላላቅ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ሚና አላቸው። 

አደይ አበባ ስታዲየም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ጠብቆ እየተገነባ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ለሀገሪቱ ስፖርት ዘርፍ ዕድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር በአብነት ጠቅሰዋል። 

በመዲናዋ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለወደፊት ትውልድ እና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ነው የተናገሩት። 

ጥራቱን የጠበቀ የስፖርት መሠረተ ልማት ዝርጋታ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በባለቤትነት ለማዘጋጀት የሚያስችል መሆኑንም አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በከተማ ልማት ተካተው መገንባታቸው በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ችለዋል።

ቀደም ሲል በከተማዋ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት በመኖሩ ወጣቶች በጎዳናዎች ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ይገደዱ ነበር  ብለዋል። 


 

አሁን ላይ የወጣቶችን ፍላጎት የሚመጥኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በብዛትና በጥራት መገንባታቸው ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ መቻሉን ተናግረዋል። 

እነዚህ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለከተማዋ ውበትና ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከታቸውም ባለፈ በአካል፣ በአእምሮ እና በጤና የበለጸገ አምራች ዜጋን በማፍራት ረገድ ትልቅ ሚና እያበረከቱ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም