የአፋር ክልል የቱሪዝም ፀጋዎች የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልል የቱሪዝም ፀጋዎች የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የሚገኙ ተፈጥሯዊና ባህላዊ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት የህዝቡን ዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
የትልቅ ሀገር ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋች ትገኛለች።
በዚህም የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግና የሀገራችንን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ጸጋዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ግዙፍ አቅም ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም በመቀየር የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ።
የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ የፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ አብዱ አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግሥት የክልሉን የቱሪዝም አቅም ለማሳደግ የመዳረሻና የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ከዚህም ባለፈ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ በሆቴል፣ በሎጅ፣ በሪዞርትና በተለያዩ የቱሪዝም አገልግሎቶች ላይ እንዲሳተፉ ምቹ የሥራ ከባቢ ተፈጥሯል ብለዋል።
የቱሪዝም ልማት ከመዳረሻዎችና መሠረተ ልማት ግንባታ ባሻገር ማኅበረሰቡን በጽዳት፣ ምግብ አቅርቦት፣ በአስጎብኝነትና በሌሎችም አገልግሎቶች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የአፋር ህዝብ ሰው አክባሪና እንግዳ ተቀባይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የክልሉን ዓመታዊ የጎብኝዎች ቁጥር ከአምስት ሺህ ወደ 40 ሺህ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።
ለዚህም በሰመራና በዙሪያዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በውሃና ኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ በመንገድና መጠለያ አገልግሎቶች ለማስተሳሰር፤ ታሪካዊና ሳይንሳዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ለጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ተስማሚ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት የመሬት አቀማመጥ፣ የግንባታ ዲዛይንና የኢንቨስትመንት አዋጭነት መረጃዎችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ባለሃብቶች የአፋር ክልል ያለውን እምቅ የቱሪዝም አቅም እንዲረዱ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ በኤርታሌ አካባቢ የጎብኝዎችን ቆይታ ለማራዘም ለሎጅ ግንባታ ፈቃድ መሰጠቱንም ገልጸዋል።
በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የፓርኩን ጥበቃ ለማጠናከርና በሰውና በዱር እንስሳት መካከል የሚከሰተው መቀራረብ ችግር እንዳይፈጥር አጥር መሰራቱን እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በአላይደጌና በሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ የሰመራ ከተማ የኮሪደር ልማት ቱሪስቶች ወደ ክልሉ ሲመጡ ምቹ ከባቢ ይፈጥራል ብለዋል።