ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት ጥቅምት 24 የተፈፀመበትን ክህደት በጽናት አልፎ በተደራጀና በላቀ መልኩ እየተገነባ ነው

ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦መከላከያ ሰራዊት ጥቅምት 24 የተፈፀመበትን ክህደት በጽናት አልፎ በተደራጀና በላቀ መልኩ እየተገነባ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የበጀትና ፕሮግራም ኃላፊ ኮሎኔል ምህረት ሽፈራው ገለጹ።

በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን ክህደት በማሰብ "እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን" በሚል መሪ ሐሳብ በባህር ዳር ከተማ መኮድ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የበጀትና ፕሮግራም ኃላፊ ኮሎኔል ምህረት ሽፈራው፤ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ የተፈፀመበትን ክህደት በጽናት አልፎ ዛሬ ላይ የላቀና የተደራጀ የሰራዊት ቁመና ማኖሩን አንስተዋል።


 

በመሆኑም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት እንዲሁም የዜጎችን ሰላም በማፅናት ሀገራዊ አደራውን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል። 

የምሥራቅ ዕዝ ግንባታና ጽሑፍ ዝግጅት ኃላፊ ሻለቃ ሰመረ እሸቱ፤ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት የመወያያ መነሻ ጽሁፍ ጥቅምት 24 ቀን የሰሜን ዕዝ በባንዳዎች ከጀርባው የተወጋበትና የተከዳበት መጥፎ የታሪክ ጠባሳ መሆኑን አንስተዋል። 


 

በመሆኑም ሰራዊቱ የከፈለውን ዋጋ በማሰብ ይህንን የጥፋትና የክህደት ድርጊት ትውልዱ በቅጡ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የስታፍ አባል ሻለቃ ዘውድነህ ሙሉጌታ እና የምሥራቅ ዕዝ ስታፍ ባልደረባ መቶ አለቃ ብርሃኑ ገመዳ፤ በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ የፈጸመው የጭካኔ ተግባር ሁልጊዜም የምናስበው ነው ሲሉ ተናግረዋል።


 

በመኮድ በተዘጋጀው የፓናል ውይይትና የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ የምሥራቅ እና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ከፍተኛ አመራሮች እና የስታፍ አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም