የኢትዮጵያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የታሪክና ቅርስ ጥበቃ ስራ ታሪክን ለመጪው ትውልድ ለማቆየት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የታሪክና ቅርስ ጥበቃ ስራ ታሪክን ለመጪው ትውልድ ለማቆየት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የታሪክና ቅርስ ጥበቃ ስራ ታሪክን ለመጪው ትውልድ ለማቆየት ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች ገለፁ።
ከካፒታል ማርኬት ተቋማት ጋር ለሶስት ቀናት የሚቆይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረገው የታንዛንያ ልዑካን ቡድን፣ የሀገሪቱን የታሪክ ሃብት፣ ባህል እና የቅርስ አጠባበቅ ጥረቶች ለመመልከት አንድነት ፓርክን እና የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባል የሆኑት ማርቲን ደብሊው፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ ታሪካዊ ኹነቶችን በስርዓት በመሰነድ ታሪክን ለትውልድ ለማሻገር የጀመረችው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው።
በተለይም ጎብኚዎች የሀገሪቱን ታሪካዊ እድገት በጥቅሉ እንዲረዱ ማስቻሉ በእጅጉ እንዳስደመማቸው ገልጸዋል።
የታሪክ መረጃዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በዲጂታል ስርዓት መቅረባቸውን አድንቀው፤ ይህም አቀራረብ ቅርሶችን ለመጠበቅ እና የታሪክ መረጃዎችን ለመጪው ትውልድ ተደራሽ ለማድረግ ውጤታማ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ልምድ ለታንዛንያ በተለይም ታሪካዊ እድገቶችን በስርዓት በመሰነድ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሀገራዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ በመተግበር ረገድ ጠቃሚ ትምህርት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
እንዲሁም የዲጂታል መድረኮች የጎብኚዎችን የታሪካዊ ቦታዎች ግንዛቤ ለማሳደግ ያላቸውን ትምህርታዊ እሴት በማጉላት፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከኢትዮጵያ አቀራረብ ትምህርት መውሰድ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው የልዑካን ቡድኑ አባል ኤሊያድ ኢ. ምንደሜ በበኩላቸው፣ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ያደረጉት ጉብኝት ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ በተለይም ታሪካዊው የዓድዋ ድል ጋር ተያይዞ የነበራቸውን ግንዛቤ እንዳሰፋላቸው ተናግረዋል።
የድል መታሰቢያውን መጎብኘታቸው ስለ ታሪካዊ ኹነቶቹ እና ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ያሳዩትን ጀግንነትና ቁርጠኝነት የበለጠ ግልጽ ግንዛቤ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
በዚህም የሀገሪቱን ታሪካዊ ቅርስ ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ያደነቁ ሲሆን፣ ዘመናዊ ቁሳቁሶቹና አጠቃላይ ሰነዶቹ ለወጣቱ ትውልድ አስፈላጊ የትምህርት ምንጭ ሆነው እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።
አክለውም ፤ያለፈው ትውልድ የከፈለውን መስዋዕትነትና ያሳየውን ፅናት ለወጣቶች በማስተማር የሀገራቸውን መፃኢ ዕድል እንዲቀርፁ የሚያደርግ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ታንዛንያውያኑ ጎብኚዎች፤ ታሪካዊ ቅርሶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የመሰነድ፣ የመጠበቅ እና የማቅረብን አስፈላጊነት አጽንኦት የሰጡ ሲሆን፣ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሃሳብ ሰጥተዋል።