ቀጥታ፡

ኮሌጁ በሚሰጣቸው ስልጠናዎች ተጠቅመን በተሰማራንበት የስራ መስክ ውጤታማ ሆነናል

ጂንካ፣ ጥቅምት 24 / 2019 (ኢዜአ) ፡-የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሚሰጣቸው አጫጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች ተጠቅመን በተሰማራንበት የስራ መስክ ውጤታማ ሆነናል ሲሉ የኮሌጁ ሰልጣኞች ተናገሩ።

የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ1994 ዓ/ም ተመስርቶ ለጂንካና ለአካባቢው ማህበረሰብ አጫጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና በመስጠት እገዛ እያደረገ የሚገኝ ኮሌጅ ሲሆን፣ አሁን ላይ 650 የሚሆኑ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል።

በኮሌጁ የሚሰጡ አጫጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን ወስደው በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ዜጎች፣ ከኮሌጁ በቀሰሙት እውቀት ተቀጥረው ከመስራት ባለፈ ሌሎችን ቀጥረው በማሰራት ረገድ ስኬታማ መሆናቸውን ይናገራሉ።


 

በጂንካ ከተማ የሚገኘው "የነገው ሰው እንጨትና ብረታ ብረት ስራ ማህበር" ስራ አስኪያጅ ወጣት ዳዊት እርኮ፣ ኮሌጁ በሚሰጣቸው አጫጭር ስልጠናዎች ተጠቃሚ መሆኑን ገልጿል። 

በድርጅቱ እየሰሩ የሚገኙ ሰራተኞችም የአቅም ግንባታ ስልጠና በማግኘት ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ተናግሯል። "ኮሌጁ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለስራችን ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል" ብሏል።


 

ኮሌጁ በተለይም ስለ ካይዘን ፍልስፍና፣ ስለ ሂሳብ አያያዝ፣ ስለ ከባድ ማሽን አጠቃቀምና ጥንቃቄ እንዲሁም ስለ ኢንተርፕሪነርሽፕ ስልጠና በመስጠት የማብቃት ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በጂንካ ከተማ የ"ባስልኤል ብረታ ብረት ስራ ማህበር" ባለቤት አቶ ጌታቸው ሙሐመድ በበኩላቸው፣ ኮሌጁ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች ለአዳዲስ ፈጠራ ስራዎች የሚያነሳሱ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ከኮሌጁ መምህራን ጋር በመተባበር የለውዝ መፈልፈያና መፍጫ ማሽን እንዲሁም የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን በጋራ በመስራት ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል። 

ማህበሩ ለኮሌጁ ተማሪዎች በተግባር ልምምድ እውቀት የሚቀስሙበትን ሁኔታ ከኮሌጁ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ካሳሁን ጌታቸው፣ ኮሌጁ በመካከለኛ ደረጃ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር በመፍታት ረገድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኮሌጁ በእርሻ፣ በከብት፣ በዶሮና በዓሳ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በሰርቬይንግ፣ በአይሲቲ እና በጋርመንት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በኢንተርፕሪነርሽፕና በካይዘን ፍልስፍና የስልጠና መስኮች ለአካባቢው ማህበረሰብ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና በመስጠት የማብቃት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በርካቶች በኮሌጁ የተሰጣቸውን የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልጠና በመጠቀም ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና የአካባቢውን ማህበረሰብ የሚጠቅም ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራ እየሰሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም