የስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ በዩኔስኮ ዝርዝር ውስጥ መካተት የቱሪዝም ጸጋዎችን ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ ለማዋል ተጨማሪ አቅም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ በዩኔስኮ ዝርዝር ውስጥ መካተት የቱሪዝም ጸጋዎችን ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ ለማዋል ተጨማሪ አቅም ነው
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፦የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ በዩኔስኮ በዓለም ጂኦፓርክ ዝርዝር ውስጥ መካተቱ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና ለመጠቀም ተጨማሪ አቅም ይሆናል ሲል የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ጂኦፓርኮች ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።
ይህም የኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችን ከማልማት ባለፈ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ብሔራዊ ድል መሆኑን የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር መግለጹም የሚታወስ ነው።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ቶፊቅ አጫሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት ጂኦፓርክ ማለት ልዩ ተፈጥራዊ የመሬት አቀማመጥ ላይ የሚገኙ ቅርሶች፣ የተለያዩ የመሬት ገጽታዎች፣ ተፈጥሮአዊ እና ታሪካዊ ቦታዎች በአንድነት ተቀናጅተው የሚገኙበት ነው።
ይህም በእሳተ ገሞራዎች የተፈጠሩ የተለያዩ ቅርጽና መልክ ያላቸው የድንጋይ አይነቶች እንዲሁም የእንስሳት ቅሪተ አካላትን አቀናጅቶ የያዘ ሥፍራ ተብሎ በዓለም የጂኦፓርክ ዝርዝር ተመዝግበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆም ጂኦፓርክ ልዩ የተራራ አፈጣጠሮች ያሉበት አካባቢ ከመሆኑ በተጨማሪ እፅዋት፣ እንስሳትን፣ እንዲሁም የሰዎችን ባህል፣ ታሪክ እና አፈ ታሪኮች አጣምሮ ያያዘ አካባቢ በመሆኑ በዓለም ጂኦፓርክ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ተናግረዋል።
ይህም የክልሉን የቱሪዝም እምቅ ፀጋዎች ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ ለማዋል ተጨማሪ አቅም መሆኑን ነው የቢሮው ሃላፊ ቶፊቅ (ዶ/ር) የገለጹት።
የስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ በሀገሪቱም ሆነ በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅና አልምቶ ለመጠቀም የራሱ ፋይዳ እንዳለውም አመልክተዋል።
ጂኦፓርኩ በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገቡ ክልሉን የሚጎብኙ ቱሪስቶችን እንዲጨምር በማድረግ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግም ያስችላል ነው ያሉት።
ስምጥ ሸለቆ በዓለም ጂኦፓርኩ ዝርዝር ውስጥ መካተቱ የባህል እሴቶቻችንን ይበልጥ በማጉላት የኢኮኖሚ አቅምን ከማሳደግ ባሻገር የምርምር እና የጥናት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ያግዛል ነው ያሉት።
ለዚህ ታሪካዊ ስኬት መመዝገብ አስተዋጾ ላደረጉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቶፊቅ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦ ፓርክ በ11ኛው የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች ካውንስል ስብሰባ ላይ ዕውቅና መገኘቱ የሚታወስ ነው።