ቀጥታ፡

በክልሉ ከዘጠኝ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ ከዘጠኝ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት  ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን የክልሉ ማዕድን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ሃላፊ አቶ ሎው ኡቡፐ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት ከዘጠኝ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

የወርቅ ማዕድን ከአምስቱ የብዝሃ ኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ያስታወሱት ሃላፊው፣ ሀብቱን በአግባቡ በማልማት የዘርፉን ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት መሠጠቱን ተናግረዋል።

መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በክልሉ ካለው እምቅ የወርቅ ማዕድን ሀብት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። 


 

በበጀት ዓመቱ ከዘጠኝ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለመላክ ታቅዶ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 1 ሺህ 530 ከሎ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን አመልክተዋል።

እንደ ሀገር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የክልሉ የወርቅ ማዕድን ሃብት ልማት ከፍተኛ መነቃቃት ማሳየቱንም የቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል።

እንደ  ሎው (ዶ/ር) ገለጻ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገው ወርቅ በአነስተኛና ከፍተኛ ኩባንያዎች የተመረተ ነው።

በመጀመሪያ ሩብ ዓመት በዘርፉ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን 1ሺህ 780 ወጣቶችን ጨምሮ ከ8 ሺህ በላይ ዜጎች በዘርፉ ተሰማርተው ተጠቃሚ እየሆኑና ህይወታቸውን እየቀየሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከክልሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ የተያዘውን የወርቅ መጠንን ለማሳካት የድጋፍና የክትትል ሥራዎች እንደሚጠናከሩም ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።


 

በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ ከተሰማሩት መካከል ወጣት ኡኩኝ ኡጉድ እና ወጣት አለሙ ጉቱማ በሰጡት አስተያየት በዘርፉ ከተሰማሩ ወዲህ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ትርጉም ባለው መልኩ እየለወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም