ቀጥታ፡

የመገጭ ግድብ ግንባታ ከመስኖ ልማት ባለፈ ለዓሳ ሃብት ልማትን ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው

ጎንደር፣ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ):- የመገጭ ግድብ ግንባታ ከመስኖ ልማት ባለፈ ለዓሳ ሃብት ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ።

የመገጭ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ባለፈው ጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን፣ የመገጭ ወንዝ ላይ የተገነባው ግድብ የግብርና ምርትን ለማስፋፋት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻልና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት የሚያግዝ ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑም ይታወቃል።

የግድቡን መጠናቀቅና አጠቃላይ ጠቀሜታውን በተመለከተ ኢዜአ የጎንደር ከተማ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ መላኩ ደምሌ ጋር ቆይታ አድርጓል።


 

የመገጭ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ከመስኖ ልማት ባለፈ ለዓሳ ሃብት ልማት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርቡ ከ125 ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩቶችን ወደ ግድቡ በማስገባት የዘርፉን ልማትና ምርታማነት የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዓሳ ሀብት ልማቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከማገዝ ባለፈ የገቢ ምንጭና የስራ እድል ማግኛ አማራጭ እንደሚሆንም አንስተዋል።


 

በዓሳ ምርት የሚሰማሩ አርሶ አደሮችን በማደራጀትና ስልጠና በመስጠት ጥራቱን የጠበቀ የአሳ ምርት ለማምረት አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በቀጣይም በግድቡ ዙሪያ ደረጃቸውን የጠበቁ የዓሳ መሸጫ ሱቆች፣ የዓሳ ማቀነባበሪያ ማዕከላትና የቤተሰብ መሠረታዊ የንግድ ሼዶች ግንባታ ለማከናወን እቅድ ተይዟል ብለዋል።


 

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ነፃነት ወርቁ (ዶ/ር)፤ ዓሳ ከፍተኛ ጥራት ያለውና የፕሮቲን ምንጭ በመሆኑ ለሰው አካላዊና አእምሯዊ እድገት ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ በመሆኑ በተለይም ለሕፃናትና ለነፍሰ ጡር እናቶች የአእምሮ እድገት ወሳኝ የሆኑትን ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲዶች፣ ካልሲየም፣ አይረንና አዮዲን ንጥረ ነገሮችን የያዘ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አርሶ አደሮች የዓሳ ምርትን በጥራትና በብዛት እንዲያመርቱ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በመሆኑም የመገጭ ግድብ የመስኖና የዓሳ ሃብት ልማት መሰረት በመሆን የሚያገለግል መሆኑን አንስተዋል።

የመገጭ መስኖ ልማት ፕሮጀክት 185 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን 17 ሺህ ሔክታር መሬት ለማልማት የሚያስችል ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም