ቀጥታ፡

ኒውክሊየር ኃይል የኢትዮጵያን የወደፊት የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝ መልኩ ለማሟላት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ) ፦ ኒውክሊየር ኃይል በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሟላት የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሽፈራው ተሊላ ገለጹ።

ምክትል ኮሚሽነሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የኢንዱስትሪ ልማት የኃይል ፍላጎትን እያሳደገው መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም ኢንዱስትሪዎችና የዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፎች ያልተቋረጠ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚፈልጉ መሆኑን አውስተው፤ ለዚህም አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው የኃይል ምንጭ የማልማትን አስፈላጊነት ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የውሃ፣ የፀሐይ፣ የንፋስና የጂኦተርማል ኃይል ልማትን ከማስቀጠል ጎን ለጎን፣ ኒውክሌር ኃይል ከፍተኛ የኃይል ማመንጨት አቅም ያለውና ያልተቋረጠ አቅርቦት ሊያረጋግጥ የሚችል አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ ግብርን ለማስፈጸም የወሰነችው የወደፊቱን የኢኮኖሚ እድገት የሚደግፍና የኃይል አቅርቦትን የሚያረጋግጥ ምንጭ ለማልማት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኒውክሊየር ኃይል ከኤሌክትሪክ ማመንጨት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በምርምር ዘርፎች ሰፊ ጥቅም የሚሰጥ ቴክኖሎጂ መሆኑን አንስተው፤ በጤናው ዘርፍ ለሕክምና ምርመራ፣ ለካንሰር ሕክምናና ለመድኃኒቶች  ምርት፤ በግብርና ደግሞ ለሰብል ምርታማነት ማሻሻያ፣ ለተባይ ቁጥጥርና ለምግብ ጥበቃ እንደሚውል አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ወደ አንድ ዓመት እየተቃረበው መሆኑን አንስተው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ተቋሙን የማደራጀት፣ የሰው ኃይልና የሥራ ቦታ የማሟላት፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ተቋሙን ወደ ሥራ የማስገባት ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራምን የሚመራ ስትራቴጂ የማዘጋጀት፣ የሀገር ውስጥ አቅም የመገንባትና በዘርፉ የሚሳተፉ ተቋማትን የማስተባበር ኃላፊነት እንደተሰጠው ጠቁመዋል።

በቀጣይ የቁፋሮና የጂኦቴክኒክ ጥናቶች በማካሄድ የማመንጫው ትክክለኛ ቦታ የሚወሰን ሲሆን፤ የኒውክሊየር ደህንነት፣ የቴክኒክ መስፈርቶች፣ የሕዝብና የአካባቢ ተስማሚነት እንዲሁም የመሠረተ ልማት ተደራሽነት በጥናቱ የሚገመገሙ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫውን የሚያስተዳድሩና የሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎችን ማሰልጠን የፕሮግራሙ ቁልፍ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ከኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ጋር ተያያዥ የሆኑ የትምህርት ሥርዓቶችን በማሻሻል፣ በዘርፉ የሚያስፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል በሀገር ውስጥ ለማፍራት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን በትምህርት፣ በምርምርና በጥናት በመደገፍ አጠቃቀሙንና የማስተዳደር አቅሙን ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ላይ የራሷን አቅም እየገነባች በመሄድ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነቷን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

በኤሌክትሪክ ማመንጨት ሂደት ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያለው ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ የምትከተለውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመደገፍ ለዘላቂ የኃይል ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም