ቀጥታ፡

በክልሉ የገበያ ማዕከላትን ለማስፋፋትና ደረጃቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቅዳሜና እሑድ ገበያ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል የግብይት ማዕከላትን የማስፋፋትና ደረጃቸውን የማሳደግ ሥራ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ወልደየስ ለኢዜአ እንዳሉት የቅዳሜና እሁድ ገበያ ኢኒሼቲቭ በገበያው ዋጋን በማረጋጋት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።


 

በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገው የቅዳሜና እሁድ ገበያ ባለፉት ጊዜያት ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፣ የግብይት ማዕከላቱን የማስፋፋት ተግባር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በ2018 የበጀት ዓመት የቅዳሜና እሑድ ገበያ ማዕከላትን ቁጥር ወደ 36 ከፍ ማድረግ መቻሉን ያስታወሱት የቢሮው ምክትል ኃላፊ፣  ዘንድሮ ተጨማሪ 20 ማዕከላትን ለማቋቋም ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 3 ማዕከላትን በማቋቋም ወደ ተግባር ማስገባት እንደተቻለ ጠቅሰው፣ በቀሪ ወራት 17 ተጨማሪ ማዕከላት በተለያዩ ከተሞች ይቋቋማሉ ብለዋል።

ቢሮው ማዕከላቱን ከማስፋፋት ባሻገር የምርት አቅርቦት መጠን እና ጥራትን በማስጠበቅ ደረጃቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

በዚህ ተግባር ገበያን በማረጋጋት የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል ከግብርና፣ ከማዘጋጃ ቤቶችና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ወይዘሮ አሰገደች አስታውቀዋል።

በገበያ ማዕከላቱ ሲሸምቱ ከነበሩ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አስራት ወልደገብርኤል ገበያው የኑሮ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገና ህብረተሰቡንም ጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመደበኛ የግብይት ማዕከላት ምርቶችን በተወሰነ ቅናሽ ለመሸመት እንዳስቻላቸው ገልጸው፣ ይህም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግሥት ለዜጎቹ በማሰብ የጀመራቸውን መሰል ኢኒሼቲቮች አጠናክሮ ቢቀጥል አቅመ ደካሞችና አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የኑሮ ጫና ያቃልላል ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።

የቅዳሜና እሑድ ገበያ ጥቅም ቀላል የሚባል ባለመሆኑ በከተማችን ውስጥ ካሉ ሁለት ማዕከላት ተጨማሪ ከፍቶ ማስፋፋት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፍጹም ዱባለ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

በሚዛን ማዕከል ጥራት ያላቸው ምርቶችን አግኝተው መሸመታቸውን ገልጸው፣ መንግስት ህዝብን ከኑሮ ውድነት ለመታደግ በየአካባቢው ያቋቋማቸው የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

 አሁን ማዕከሉ የሚገኝበት ቦታ አማካይ በመሆኑ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም እና ሌሎች የግብርናና የፋብርካ የፍጆታ ምርቶችን በቀላሉ እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም