ቀጥታ፡

ሱ-35 ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች የኢትዮጵያን ወታደራዊ አቅም እና ቀጣናዊ ሚና የሚያሳድጉ ናቸው-እስራኤላዊው ጋዜጠኛ ኤዲ ኮሄን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24 /2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሩሲያ የተቀበለቻቸው ሱ-35 (Su-35) ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ወታደራዊ አቅም እና በቀጣናው ያላትን ሚና በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ መሆናቸውን የእስራኤሉ ቻናል 14 ጋዜጠኛ እና ተመራማሪ ኤዲ ኮሄን ገለጹ።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) ባለፈው ሳምንት ከሩሲያ ተረክባለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት በሩሲያ ተገኝተው የጦር ጄቶችን በተረከቡበት ወቅት ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይሏ እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እያላበሳት ይገኛል ብለዋል።


 

ይህ ታሪካዊ ስኬት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ወደፊትም የጋራ ደህንነታችንን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት እንድንቀጥል ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

የእስራኤሉ ቻናል 14 ጋዜጠኛ እና ተመራማሪ ኤዲ ኮሄን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ የነበሩባትን መሰናክሎች በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶቿ እና በጠንካራ ዓለም አቀፍ ግንኙነቷ በመሻገር ከሩሲያ ጋር የነበራትን ስምምነት በተሳካ ሁኔታ መፈጸም መቻሏን ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን የመምራት እና ስትራቴጂካዊ ጥቅሟን የማስከበር አቅሟ ማደጉን በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሩሲያ የተቀበለቻቸው ሱ-35 (Su-35) ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ወታደራዊ አቅም እና በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

የግብፅና የዐረብ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ወታደራዊ ዕድገት በቅርበት እየተከታተሉት እንደሚገኙና አገሪቱ አየር ኃይሏን ማጠናከሯ በግብፅ በኩል ትልቅ ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኮሄን የግብፅን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተችተዋል።

ግብጽ ቀጣናዊ ለውጦችን የሚመጥን ግልጽ የፖለቲካ ራዕይ እንደሚጎድላት ገልጸው፤ እየጨመረ የመጣው የውስጥ ኢኮኖሚ ውጥረት እና የፖለቲካ ፈተናዎች የግብፅ አመራር አገሪቱን የመምራት ብቃት ላይ ጥያቄዎችን እያስነሳ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ዘመናዊ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ሆናለች።

ይህም ሀገሪቷ የጠላት ጥቃትን የመከላከልና የማክሸፍ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ እንድታጠናከር አስችሏታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም