የታሪክ ማህደር የተሰነደባት፣ የተፈጥሮ ውበት የሞላባት ሀገር - ኢዜአ አማርኛ
የታሪክ ማህደር የተሰነደባት፣ የተፈጥሮ ውበት የሞላባት ሀገር
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ መሰረት፣ የታሪክ ማህደርና የተፈጥሮ ውበት ማሳያ የሆነች ሀገር ነች። በእምቅ የቱሪዝም ሃብት፣ በኢንቨስትመንትና በአረንጓዴ አሻራ ልማትም ዓለም የመሰከረላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ታሪክና ተፈጥሮ፣ ባህልና ስልጣኔ፣ የቀደመ ክብርና የወደፊት ተስፋ በአንድ ላይ የተሰናሰሉባት የተስፋዋ ምድር መሆኗም ይታወቃል። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ የጥንት ታሪክ አሻራዎችን ከያዙ የአርኪዮሎጂ ቅርሶች እስከ ዘመናትን ተሻግረው የዘለቁ የስልጣኔ አሻራዎች እምቅ ሃብት ያሉበት ምድረ ቀደምት ሀገርም ነች።
የኢትዮጵያ የታሪክ ምዕራፍ ከሰው ልጅ መገኛነት ጋር በጥልቅ የተያያዘ ሲሆን በአፋር የተገኙ የጥንት የሰው ቅሪተ አካላትና የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። የአክሱም ስልጣኔ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር ቤተመንግሥቶች፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ሐረር ጥንታዊ ከተማና ሌሎችም ታሪካዊ ቅርሶች የሀገሪቱ የስልጣኔ ምልክቶች ናቸው።
ከታሪካዊ ቅርሶቿ ባሻገር ከዳሎል የሙቀት ምድር እስከ ራስ ዳሸን ከፍታ፣ ከሰሜን ተራሮች እስከ ደቡብ ለምለም ደኖች፣ ከጣና ሐይቅ እስከ አባይ፣ ኦሞና አዋሽ ወንዞች እስከ ኮንሶ መልካአ ምድሮች የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቷ የሀብትና የውበት መገለጫ ሆነው ቀጥለዋል። የሰሜን ሰማይ ተደግፈው የቆሙ የሚመስሉ ተራሮቿ፣ ጥልቅ ሸለቆዎቿ፣ የሐይቆቿና የዱር እንስሳት ሀብቷ ለቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሃብቶች ናቸው። በዩኒስኮ ተመዝግበው የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶች የሚገኙባት አስደናቂ ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ምድር በመሆኗም በዓለም ላይ የተለየ ስም አላት። ቡና ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የማኅበራዊ ትስስር መሰረት፣ የእንግዳ አቀባበል ባህላዊ መገለጫዋ መሆኑም ይታወቃል። በመሆኑም የቡና ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያን የባህልና የማንነት መገለጫ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆን ትታወቃለች። የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በማስተናገድ የአፍሪካ ድምፅ የሚሰማባት የውይይትና የትብብር መድረክ ሆና እያገለገለችም ትገኛለች። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች የሚካሄዱባት ተመራጭ ከተማ ሆናም ቀጥላለች።
በስፖርት ዘርፍም በተለይም በረጅም ርቀት ሩጫ የዓለምን የስፖርት ታሪክ የቀየሩ ታዋቂ አትሌቶችን አፍርታለች። ከጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ እስከ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፤ ከደራርቱ ቱሉ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር ስማቸውና ዝናቸው በዓለም የሚታወቁ አትሌሎችን አፍርታለች። ይህም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበት ብቻ ሳይሆን የአረንጓደው ጎርፍ የስፖርት መሰረትና የገር ዲፕሎማሲ መገለጫ መሆናቸውን የሚያመላክት ሆኗል።
በአካባቢ ጥበቃና በዘላቂ ልማት ዘርፍም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ትልቅ ጥረት እያደረገች ያለች ሀገር መሆኗን የሚያመላክት ነው። ከ2011 እስከ 2018 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አስደናቂ ተግባር ፈፅማለች።
በታዳሽ ኃይል ልማትም ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም እያለማችና እየተጠቀመች ትገኛለች። የውሃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይና የጂኦተርማል ኃይል ሀብቶቿን በማልማት የሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ለጎረቤት አገራት ኤሌክትሪክ በማቅረብ የኃይል ትስስር ማእከል ሆና እያገለገለች ትግኛለች።
በመሆኑም የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶች በማስተዋወቅና ልማትን ይበልጥ በማስፋፋት፣ ታሪካዊና የተፈጥሮ ቅርሶችን በመጠበቅ የዓለም የስህበት ማእከል ሆና እንድትቀጥል ማድረግ ይገባል። የታሪክ ማህደርነቷ፣ የተፈጥሮ ውበቷ፣ የታሪክና የባህል እሴቷ ተጠብቆና ተሰንዶ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሰራ ይገኛል።