የተጀመሩትን የልማት ስራዎች ለማስቀጠል የተገኘውን ሰላም በማጽናት ተግባር ውስጥ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመሩትን የልማት ስራዎች ለማስቀጠል የተገኘውን ሰላም በማጽናት ተግባር ውስጥ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አምቦ፤ ጥቅምት 24/2019(ኢዜአ)፡- በከተማው የተጀመሩትን የልማት ስራዎች ለማስቀጠል የተገኘውን ሰላም በማጽናት ውስጥ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ደጄኔ ተረፈ ገለጹ፡፡
በየደረጃው ያሉ የፖሊስ አባላት፣ የሥራ ሃላፊዎች እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የተሳተፉበት የሰላም ምክክር መድረክ ዛሬ በአምቦ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ደጄኔ ተረፈ እንዳሉት፤ የከተማው ህብረተሰብ ዋነኛ ፍላጎት የሕግ የበላይነት ተከብሮ ከሰላም ስጋት ነፃ ሆኖ የልማት ሥራዎችን ማከናወን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማው ሰላም እንዳይኖር የሚሰሩ አካላትን ህብረተሰቡ በአንድነት ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጎን በመቆምና በአንድነት በመደራጀት አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።
በተለይም የጸረ ሰላም ቡድኖች ፍላጎት እንዳይሳካና የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን በማድረጉ ረገድ ህዝቡ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ዋነኛ ዓላማ በዜጎች ተሳትፎ ሰላምን በማጽናት ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ጠንካራ ሀገር መገንባት መሆኑን በመጥቀስ፤ ሕብረተሰቡ ሰላሙን በመጠበቅና የከተማዋን የልማት ሥራዎች በማፋጠን የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የከተማው ነዋሪ አቶ ፈይሳ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ሰላምን ለማስፈን የፖሊስ፣ የሚሊሻ እና የጋቸና ሲርና አባላት በአንድነት ከህብረተሰቡ ጋር በመቆምና በመተባበር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የተገኘውን ሰላም በማጽናት ውስጥ የህብረተሰቡ በተለይም የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን በማንሳት፤ ሰላምን በመጠበቅ በከተማው እየተከናወኑ ያሉትን የልማት ስራዎች አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል፡፡
የከተማውን ሰላም በመጠበቅ እየተሰሩ ያሉትን የልማት ስራዎች እንዴት ማገዝ እንዳለባቸው ከውይይቱ ሰፊ ትምህርት ማግኘቷን የተናገረችው ደግሞ ወጣት ውባየሁ ጌታነህ ናት፡፡
ወጣቷ አክላም ሁሉም የከተማው ህብረተሰብ በመተሳሰብና በአንድነት በመቆም በከተማው የሰፈነውን ሰላም በመጠበቅ የአምቦን ከማሳደግ አልፈን ሀገራችን የያዘችውን የእድገት ጎዳና ማፋጠን ይገባናል ብላለች፡፡