የሸገር ከተማ አስተዳደር የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በሀገራዊ እድገት ውስጥ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል -ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ አስተዳደር የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በሀገራዊ እድገት ውስጥ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል -ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)
ሸገር ፣ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፡- የሸገር ከተማ አስተዳደር የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ የከተማው ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) ገለጹ።
በሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ክፍለ ከተማ አንዶዴ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማሳን በዘር የመሸፈን መርሃግብር ተካሄዷል።
የከተማው ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ግብርናን ማዘመን የማህበረሰቡን ህይወት ከመቀየር ባሻገር ለሁለገብ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነው፡፡
በተለይም በከተማ ደረጃ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት ዓመቱን ሙሉ ማምረት እና የሰብል ምርትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማው በዘመናዊ ዘዴዎች በማምረት ላይ ትኩረት በማድረግ በምግብ ራስን ለመቻልና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ አርሶ አደሩም የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን በመጠቀም ወደ ምርት እየገባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመሆኑም የሸገር ከተማ አስተዳደር የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
የከተማው ምክትል ከንቲባ እና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ መሪድ ድምሩ በበኩላቸው፤ በሸገር የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ግብርናውን በማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማዋ አርሶ አደሮችን በማቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እና ሽግግርን እውን እያደረገች ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በተለይም ባለፉት ዓመታት ከውጭ ይገባ የነበረው ስንዴ አሁን በሸገር ከተማ በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት መቻሉ በግብርና ዘርፍ የታየውን ለውጥ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የመስኖ ልማት የድህነት ዑደትን በመስበር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ራስን የመቻል እቅድ እውን የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ዓመት ከመስኖ በከተማው የተሻለ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የገላን ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ ኢሳ ጉዬ፤ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መካከል የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ ራስን መቻል ላይ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም እንደገላን ክፍለከተማ የስንዴ ምርትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።