ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ እና አህጉራዊ ትስስር መሠረት ጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ እና አህጉራዊ ትስስር መሠረት ጥሏል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኃይል አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር መሠረት መጣሉን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ድንቁ ስዩም (ዶ/ር) ገለጹ።
36ኛው የአፍሪካ ሃይድሮ ሲምፖዚየም «በአፍሪካ የማገገም አቅም ያለው የውሃ ሀብት እና የውሃ ሃይል ደህንነት» በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ለታዳሽ ሃይል ልማት ያላትን ቁርጠኝነት በህዳሴ ግድብ አረጋግጣለች።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሀብትን ለዘላቂ ልማት በመጠቀም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ምቹ ምህዳር የመፍጠር ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።
በዚህም አፍሪካን በሃይል አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር መሰረት መጣሉን አስገንዝበዋል።
በአረንጓዴ አሻራ እና በተፋሰስ ልማት ስራዎች የተከናወኑ ተግባራት ለቀጣናው ሀገራት ጭምር ምሳሌ የሆነና ለአየር ንብረት ለውጥ አስቻይ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሲምፖዚየሙ የአፍሪካን የውሃ ልማት እና የሃይል አቅርቦት ትስስር ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዘርፉ የሚፈጠር የልማት ትብብርን ለማጠናከር እና የአሰራር ስርዓትን ለማሻሻል አይነተኛ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) ዋና ጸሐፊ ክሌቨር ጋቴቴ በበኩላቸው፣ በአፍሪካ እየጨመረ የመጣውን የሃይል ፍላጎት ለማሟላት ዘርፉን በመሰረተ ልማት የማጠናከር ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በኢንዱስትሪ፣ በቀጣናዊ ንግድ እና ስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም አህጉሪቱ ያላትን እምቅ የውሃ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል የሃይል አማራጭን ማሳደግ እንደሚገባ አብራርተዋል።
በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው የውሃ ልማት ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ከዘርፉ የሚገኘውን የጋራ ተጠቃሚነት ለማጠናከር በጋራ መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካን የውሃ ልማትና የሃይል አቅርቦት ትስስር ላይ ያተኮረው 36ኛው የአፍሪካ ሃይድሮ ሲምፖዚየም ለቀጣይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።