አመራሩ የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህር ዳር፤ጥቅምት 24/2019(ኢዜአ)፦አመራሩ በሁሉም ዘርፎች ምርታማነትን በማሳደግና የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አሳሰቡ።
የአማራ ክልል የ2019 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ እንዳሉት፣ የክልሉን የተፈጥሮ ሀብትና የመልማት አቅም አሟጦ በመጠቀም ይገባል።
የመደመር መንግሥት የአመራሩንና የተቋማትን የመፈጸም አቅም በማሳደግ ሥራዎችን ከረጅም ጊዜ ግብና ፍላጎት አንጻር ታሳቢ በማድረግ እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ወራት በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን እንደተቻለ አንስተው፣ በቀጣይ ወራት በላቀ ንቅናቄና ቅንጅት ተግባራትን ዘላቂ ለውጥ በሚያመጣ አግባብ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
አመራሩ የአፈጻጸሙን ጥንካሬና ድክመቶች በመለየት፣በሁሉም ዘርፎች ምርታማነትን በማሳደግና የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳብራሩት፣ብልጽግና ፓርቲ በሁሉም ዘርፎች የላቀ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
በተለይም ለግጭት ምክንያት የሆኑ የተዛቡ ትርክቶችን በማረም፣ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ እና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል በማዳበር ረገድ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣በአገልግሎትና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸው በትምህርት፣በጤና፣ መሠረተ ልማትን በማስፋፋትና በሌሎች ዘርፎችም ዕድገት መመዝገቡን አቶ ይርጋ ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ አዲስ የሥራ ባህል መገንባቱን ያመለከቱት ኃላፊው፣ በዚህም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃት ረገድ ፓርቲው የመሪነት ሚናውን በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
በቀጣይ ወራትም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማረጋገጥ፣ የሴቶችንና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግና ሕገ ወጥነትንና ሙስናን በመከላከል ረገድ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
አመራሩ ወቅታዊ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ፈጥሮ ተግባራትን በላቀ ንቅናቄ መተግበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የፓርቲና የመንግሥት የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።