የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶች እና ረቂቅ ደንብ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶች እና ረቂቅ ደንብ አጸደቀ
ድሬደዋ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 4ተኛ የስራ ዘመን 1ኛ አመት የመጀመሪያ አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችና ረቂቅ ደንብ በማፅደቅ ተጠናቀቀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎችና ምክትል ሰብሳቢዎች እንዲሁም የፅህፈት ቤት ኃላፊ ሹመቶችን አጽድቋል።
በዚሁ መሰረት ፦
-ወይዘሮ ከሪማ አሊ የምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
-ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌን የግብርና፣ ተፈጥሮ ሃብት እና የአካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣
-ወይዘሮ ሚስራ አብደላ የሴቶችና ወጣቶች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፣
-አቶ ቢቂላ ታደሰ የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ተሹመዋል።
ጉባኤው በተጨማሪም ምክትል ሰብሳቢዎችና አባላት ሹመትን ያፀደቀ ሲሆን የአስተዳደሩ ይግባኝ ሰሚና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ምክትል ፕሬዝዳንቶች ሹመትንም አፅድቋል።
ከነዚህ በተጨማሪም በድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደም አቅራቢነት አምስት አባላት ያካተተ የድሬዳዋ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሹመትንም አጽድቋል።
ከንቲባው የድሬዳዋ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ የቦርድ ሰብሳቢዎች እና አባላትን ያቀረቡ ሲሆን የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ የቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ማሞ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን ተሹመዋል።
ምክር ቤቱ ከዚሁ ጎን ለጎን የድሬዳዋ አስተዳደር ንብረት ታክስ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ጫልቱ ሁሴን የፀደቀው ረቂቅ የንብረት አስተዳደር ታክስ ከከተማዋ ዕድገትና የህዝብ መጨመር ጋር ተያይዘው ለሚቀርቡ ማህበራዊ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
ገቢን ከየዘርፉ በአግባቡ በመሰብሰብ ከከተማው ዕድገት ጋር የሚጣጣም መሠረተ ልማት ለመዘርጋት፣ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍጥነት ለመመለስ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮችና አባላት መደራጀት ምክርቤቱ ለሚያካሂደው እና ለተጣለበት ታላቅ የህዝብ ተልዕኮ መሳካት ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል።