ኢትዮጵያ ወሳኝ የማዕድን ሃብቷን ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ማዋል የሚያስችል አቅም እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ወሳኝ የማዕድን ሃብቷን ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ማዋል የሚያስችል አቅም እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ወሳኝ የማዕድን ሃብቷን ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ወጪ ንግድ ስትራቴጂክ ተወዳዳሪነት ማዋል የሚያስችል አቅም እየገነባች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው ማዕድናት ላይ የፖሊሲ ምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ወርቃለማው ደስታ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ፣ አጠቃላይ እና ዘላቂ ኢኮኖሚ የመገንባት ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ ሰንቃ እየሠራች ትገኛለች።
በዚህ ሂደት ውስጥ የማዕድን ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከጥቂት ዘርፎች ጥገኝነት ለማላቀቅ፣ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስትራቴጂካዊ ዘርፍ ተደርጎ መለየቱን አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ወሳኝ ማዕድናትን ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንና ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለመጠቀም ትኩረት አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚደረገውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለማጠናከርም የማዕድን ዘርፉን እንደ ዋና ስትራቴጂካዊ መሣሪያ እንደምትጠቀምበት አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ ዝቅተኛ ካርቦንና ለአየር ንብረት ለውጥ ወደማይበገር ኢኮኖሚ እያደረገ ያለው ሽግግር የወሳኝ ማዕድናትን አስፈላጊነት እጅግ ከፍ እንዳደረገው አንስተዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ እነዚህን ማዕድናት ማልማቷ አረንጓዴና ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለያዘችው ሀገራዊ ዓላማ ትልቅ አቅም እንደሚሆናት ገልጸዋል።
መድረኩ የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ በወሳኝ ማዕድናት ላይ የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲዋሳ አብዲላሂ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ወርቅ፣ ፖታሽ እና ሌሎች በርካታ ማዕድናትን ያቀፈች እጅግ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በወሳኝ ማዕድናት ላይ የሚያደርጉትን የጋራ ሥራ ማጠናከራቸው ሁለቱንም ወገኖች በጋራ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አንስተዋል።
በአውሮፓ ህብረት ልዑክ የግሪን ዲል ቡድን መሪ ጁልያ ዌይቨቤር፤ ወሳኝ ማዕድናት ለንጹህ ኃይል፣ ለዲጂታል ኢኖቬሽን፣ ለሕክምና ቴክኖሎጂ እና ለዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ዋና ግብአቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የወሳኝ ማዕድናት ሀብት እና ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል አቅም ያላት በመሆኗ፣ ለአውሮፓ ህብረት ወሳኝ እና ልዩ የአጋርነት ሚና ያላት ሀገር መሆኗን አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማቶች፣ የማዕድን ዘርፍ ተመራማሪዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው ።