የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት መሻሻል ለአስቸኳይ ሕክምና ምላሽ አሰጣጥ ስኬት መሠረት ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት መሻሻል ለአስቸኳይ ሕክምና ምላሽ አሰጣጥ ስኬት መሠረት ሆኗል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት መሻሻል ለአስቸኳይ ሕክምና ምላሽ አሰጣጥ ስኬት መሠረት መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው 7ኛው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ጉባኤው እስከ ጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ 7ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዓለም አቀፍ የአስቸኳይ ሕክምና ቡድኖች ጉባኤ እንድታስተናግድ መመረጧ ታላቅ ክብር ነው።
ጉባኤው በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ ከቦታ ለውጥ በላይ አፍሪካ በአለም አቀፍ የአስቸኳይ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ረገድ አቅሟን፣ አመራሯንና ኃላፊነቷን እያሳደገች መሆኗን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአደጋ ጊዜ የሕክምና ድጋፍ ቡድን መመስረቷን ገልጸው፤ ይህም ውጤታማ የአስቸኳይ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ማንኛውም አደጋ ከመከሰቱ በፊት በሚደረግ ዝግጅት እንደሚጀምር በመገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ በአገር ውስጥ የተለያዩ ተልዕኮዎችን ማከናወኑንና በኢትዮጵያ በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ማኅበረሰቦች አገልግሎት መስጠቱን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ያቀፈ ብሔራዊ የምላሽ ቡድን መሰማራቱንና አጋርነታቸውን ከድንበር ባሻገር ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋሚ የአስቸኳይ ሕክምና ቡድን በዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የደረጃ አንድ እውቅና እንደተሰጠው ገልጸው፤ በዚህም በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ከመጀመሪያዎቹ የሲቪል የአስቸኳይ ሕክምና ቡድኖች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ሕክምና ምላሽ አሰጣጥ ስኬት አጠቃላይ ከጤና ሥርዓቱ መሻሻል ጋር የተያያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው፣ የአስቸኳይ ሕክምና ቡድኖች በዓለም አቀፍ የጤና ድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጪ የሰው ኃይል ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከ42 አገራት የተውጣጡ 77 ቡድኖች በዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ምደባ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋሚ የአስቸኳይ ሕክምና ቡድን እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
ይህም በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ምደባ ያገኘ የመጀመሪያው የሲቪል የአስቸኳይ ሕክምና ቡድን መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ማንኛውም ሀገር የጤና ድንገተኛ አደጋን ብቻውን እንዳይጋፈጥ በቀጣይነት መሥራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ ያኩብ ጃናቢ በዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአህጉሪቱ በሚካሄደው ጉባኤ አፍሪካ እንደ እንግዳ ተሳታፊ ሳይሆን፣ እንደ መሪና የውይይቱ አጀንዳ ቀራጭ ሆና መገኘቷን ያመለክታል ብለዋል።
አፍሪካ በየዓመቱ ከፍተኛ የሕዝብ ጤና አደጋዎች እንደሚጋጥሟት ጠቁመው፣ መንግሥታት የገቡትን ቃል ኪዳን ወደ ብሔራዊ ዕቅድ እንዲቀይሩም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ ፣ ጉባኤው ለልምድ ልውውጥ፣ ለትብብርና ለጋራ እርምጃ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ተቋማት፣ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመሥራት ይህንን አጀንዳ በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።