ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን የደረሱ ሰብሎች ከምርት ብክነት በጸዳ ሁኔታ እየተሰበሰቡ ነው

ወልቂጤ ፤ጥቅምት 24 /2019(ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ከምርት ብክነት በጸዳ ሁኔታ እየሰበሰቡ መሆናቸውን የዞኑ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

በዞኑ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና በተለያዩ ምክንያቶች በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በወቅቱ እንዲሰበሰብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በመኸር ወቅት የለሙና የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ከብክነት በጸዳ መልኩ እየሰበሰቡ ነው።

በዞኑ በእኖር ወረዳ የገረንምቦ ቀበሌ አርሶ አደር ደሳለኝ ወልዴ በመኸር ወቅት የዘሩትን የበቆሎ ምርት ሰብስበው በመከመር አሁን ላይ የጤፍ ምርት ከአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር እየሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል። 

የተሰበሰበው ሰብል  ወቅቱን ላልጠበቀ ዝናብ እንዳይጋለጥ በተገቢው መንገድ በመከመር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በወረዳው የሆርበትናዚዞ አርሶ አደር ፍቃዱ ሀሰና በበኩላቸው፣ የቤተሰብ እና የደቦ አደረጃጀትን በመጠቀም በበቆሎ እና በጤፍ ምርት አሰባሰብ ወቅት የሚደርሰውን የምርት ብክነት ለመቀነስ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በምርት አጨዳና አሰባሰብ ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን ብክነት ለመቀነስ የሚያስችሉ የግንዛቤ ስራዎች በየደረጃው ባሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

በአበሽጌ ወረዳ የጣጤሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብራር ሽኩር በመኸር አዝመራ ያለሙት የጤፍ ምርት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳይጎዳና ሳይባክን ለመሰብሰብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። 

የምርቱ ሁኔታ ያማረና ተስፋ ሰጪ መሆኑን በመግለጽ፣ ብክነት እንዳይከሰት የደረሱ ሰብሎችን በደቦ በወቅቱ መሰብሰብ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀምና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ፣ በዞኑ በመኸር ከተሸፈነው ከ178 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ40 ሺህ ሔክታር የሚልቀው ሰብል መሰብሰቡን ጠቅሰዋል። 


 

በዚህ ወቅት በዋናነት የበቆሎና የጤፍ ምርት ለአጨዳ መድረሱን በመግለጽ፣ የምርት ብክነት እንዳይኖር የቤተሰብ ጉልበትንና አደረጃጀቶችን በመጠቀም በጥንቃቄ እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሳምንት በኋላ ለአጨዳ የሚደርሱት የስንዴና የገብስ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ብክነትን ለመቀነስ አርሶ አደሩ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽነሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚያውል አውስተዋል።

በውቂያ ወቅትም በቆሎን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን ለመውቃት የዞኑ አስተዳደር መውቂያ ማሽኖችን በማቅረብ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመኸር ከለማው ሰብልም ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም