ቀጥታ፡

በዘንድሮው የመኸር አዝመራ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - አርሶ አደሮች

አዳማ፣ ጥቅምት 24/2019(ኢዜአ) ፡-በዘንድሮው የመኸር አዝመራ የተሻለ ቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮችን በመጠቀማቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የሄጦሳና ጥዮ ወረዳዎች አርሶ አደሮች ገለፁ።

ለኢዜአ አስተያየት ከሰጡት አርሶ አደሮች መካከል የሄጦሳ ወረዳ ኦዳ ጂላ ቀበሌ ነዋሪ ቦኪ ዲንቁ በመኽር አዝመራው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በኩታ ገጠም ካለሙት በተጓዳኝ አንድ ሄክታር መሬት በምርጥ ዘር ስንዴ ማልማታቸውን ተናግረዋል።

የሰብሉ አያያዝ በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም አርሶ አደር ቦኪ ጨምረው ገልጸዋል።

በተለይም ሜካናይዜሽን ተጠቅመንና የባለሙያዎችን እገዛ ተከትለን በመስመር በመዝራታችን ሰብሉ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ምርት ይዟል ብለዋል።

በየዓመቱ አዳዲስ የስንዴ ምርጥ ዘርና ቴክኖሎጂ ተጠቅመው እንደሚዘሩና በዚህም የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሄጦሳ ወረዳ ኦዳ ጂላ ቀበሌ  አርሶ አደር ነጋሽ ለማ ናቸው ።


 

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀማቸው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ የተሻለ ልምድና ክህሎት እንዳገኙ የሚናገሩት አርሶ አደር ነጋሽ፤ በዘንድሮው ዓመት ጉቱና ቁሉምሳ የሚባሉ የስንዴ ምርጥ ዘር በመውሰድ ዘርተው በአሁኑ ወቅት አዝመራው በጥሩ ይዘት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በጥዮ  ወረዳ ኦዳ ደዋታ ቀበሌ  አርሶ አደር ጎሳ ናሞ በበኩላቸው ምርጥ ዘር ወስደው በኩታ ገጠም በማልማት  ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ መገኘቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሰብሉ እየደረሰ በመሆኑ ሜካናይዜሽን ተጠቅመው ለመሰብሰብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አርሶ አደር ጎሳ፤ የኮምባይነር አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥማቸው ከወዲሁ ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚኙ ተናግረዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን በዞኑ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች ለምተዋል ያሉት ደግሞ የደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል  ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ቃሶ ናቸው።


 

በዞኑ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመርና የምግብ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

በተለይም የአፈር ለምነት ለመጠበቅና የተሻለ ምርት ለማግኘት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት አርሶ አደሩ መጠቀሙን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ  የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ አዳዲስ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎች፣ ሙያዊ የሰብል ልማት እገዛና ድጋፍ በተሻለ ሁኔታ የተጠቀምንበት ወቅት ነበር ብለዋል።

በዚህም የዋና  ዋና ሰብሎች ቁመና ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ምርት መያዙን አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል።

በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ለ2018/19 ዓ.ም የምርት ዘመን በመኽር አዝመራ ከለማው መሬት ከ96 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም