ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን የደረሰ የመኸር ሰብል እየተሰበሰበ ነው

ደብረ ማርቆስ፣ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ጎጃም ዞን የደረሰ የመኸር ሰብልን በወቅቱ በመሰብሰብ ምርትን ከብክነት ለመታደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢአለ አለኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በምርት ዘመኑ በዞኑ ከ688 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል።

አርሶ አደሩ አዳዲስ የግብርና አሰራሮችንና ግብአቶችን በአግባቡ ተጠቅሞ ካለማው መሬት ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና በተባይ እንዳይጎዳ አርሶ አደሩ በደቦና በልማት ቡድን  ምርቱን ፈጥኖ እንዲሰበስብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በኩታ ገጠም እርሻ በስፋት በለሙ አካባቢዎች ከ40 በላይ ኮምባይነሮችን በማስገባት ሰብሉን ፈጥኖ ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

እስካሁንም ከ82ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል  መሰብሰቡን ያመለከቱት ቡድን መሪው፣ በሰብል ስብሰባው 150 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳፋቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ደብረኤሊያስ ወረዳ የወርቅማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደግሰው ይታይህ እንዳሉት ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን የደረሱ ሰብሎችን በደቦ እየሰበሰቡ ይገኛሉ።

ሰብሉን በጊዜው መሰብሰባቸው በእንስሳትና በአዋፍ እንዳይጎዳ ከማድረጉ በተጨማሪ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብም ለመከላከል እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።

በአዋበል ወረዳ የጎደራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገነት በላቸው በበኩላቸው የደረሱ ሰብሎች በተለያየ ምክንያት ለጉዳት እንዳይዳረጉ በደቦ መሰብሰብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን ከግማሽ ሄክታር በላይ የጤፍ ሰብል እንደተሰበሰበ ጠቁመው ይህም መሬቱን መልሶ በመስኖ ለማልማት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ በምርት ስብሰባ ወቅት የምርት ብክነት እንዳይከሰት ከግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ሙያዊ ድጋፍ መሰረት ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉ መሆናቸወንም ተናግረዋል። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም