በጠላት የማይደፈር ጀግና ሰራዊት - ኢዜአ አማርኛ
በጠላት የማይደፈር ጀግና ሰራዊት
የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚለካው በሀብቷና በተፈጥሮ ጸጋዎቿ ብቻ ሳይሆን በሚገጥሟት ፈተናዎች ወቅት ሉዓላዊነቷንና ሕልውናዋን በሚጠብቁ ተቋማት ጥንካሬ ጭምር ነው። ለዚህ ደግሞ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በረጅም የታሪክ ሂደት ውስጥ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና የዜጎችን ደኅንነት በመጠበቅ በቆራጥነትና ጀገንነቱ የሚታወቅ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል የሰሜን እዝ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተፈፀመበት ክህደት መቼም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም። በወቅቱ የተፈጸመው ክህደት በሰራዊቱ ላይ አረመኔያዊ ድርጊት ከመፈፀምም ባሻገር ኢትዮጵያን ያለ ጠባቂ ጋሻ እና መከታ የማስቀረት እኩይ ተግባር ነበር። ይሁን እንጂ በጀግንነቱ የሚታወቀውና ህዝባዊ መሰረት ያለው መከላከያ ሰራዊት በመስዋእትነት ሀገሩን ከጥፋት ታድጓታል። በሀገር ፍቅር፣ በታማኝነት፣ በሙያዊ ኃላፊነትና በሕዝብ አለኝታነቱ የሚታወቀው ሰራዊት እምቢ ለሀገሬ በማለት የተደቀነውን የጥፋት እቅድ አክሽፎታል። በወቅቱ ተደቅኖበት የነበረውን ከባድ ፈተና በጽናት በማለፍ ሀገሩን በጽናት አስቀጥሏል።
የጥቅምት 24ቱ ክስተትና የተመከተበት መንገድም የኢትዮጵያ ሕልውና በካሃዲዎች የማፍረስ መሆኑን ያረጋገጠ፤ በሀገር ክብርና ሉአላዊነት በቆመው መከላከያ ሰራዊትና ሀገር ወዳዱ ህዝብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው። ከዚህ ክህደት የምንማረውም የሕዝቡና የመከላከያ ሰራዊት ትስስር ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ነው። ሰራዊቱ የሕዝብ ልጅ፤ ሕዝቡም የሰራዊቱ መሠረታዊ አለኝታና ዋስትና መሆኑ በተግባር ታይቶበታል።
በእነዚህ ፈተና ወቅት የተከፈለው መስዋዕትነትም የሀገር የጀግንነት ውርስ መሆኑ ተመላክቷል። ለሀገራቸው ክብርና ለሕዝባቸው ደኅንነት ሕይወታቸውን የሰጡ ጀግኖች የታሪክ አሻራቸው በየትውልዱ የማይረሳ ታሪክ ሆኖ አልፏል። በየትውልዱ ሀገር የሚረከቡ ወጣቶች ከዚህ ጀግና ሰራዊት ሀገር ወዳድነትን፣ ለህዝብና ለሀገር መሞትን የሚማሩበት ነው።
የተጋረጠውን ፈተና ማለፍ ብቻ ሳይሆን ከችግሩ ትምህርት በመውሰድ የበለጠ ጠንካራ፣ በሙያ የበቃ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና ለማንኛውም ተልእኮ ዝግጁ የሆነ ሰራዊት የመገንባት ሂደትን ያስተማረ ክስተት ሆኗል። በዚህም የሰራዊቱ የሰው ኃይልና ሙያዊ ብቃት፣ የተቋማዊ አደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ አቅምና ግዳጅ የመፈፀም ብቃት የላቀ ማድረግ እንደሚገባ ትምህርት በመውሰድ በጠላት የማይደፈር፣ ዘመናዊ፣ ጀግና እና ጠንካራ ሰራዊት መግንባት ተችሏል።
በመሆኑም የጥቅምት 24 ታሪክ የክህደትና የመከራ ትዝታ ብቻ ሳይሆን ከከባድ ፈተና በኋላ የመቆም፣ የመማርና የመጠናከር አቅምን ያሰባሰበ ነው። የከሃዲዎች እኩይ ዓላማ ቢኖርም የኢትዮጵያ ሕልውና በጀግኖቿ መስዋዕትነትና በሕዝቡ አለኝታነት የሚቀጥል መሆኑንም ያረጋገጠ ነው።