በትግራይ ክልል ለሠራተኞች ዛሬ ደመወዝ መከፈል ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ለሠራተኞች ዛሬ ደመወዝ መከፈል ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2019 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ከቀን ወደ ቀን ሰላምና መረጋጋት ሙሉ በሙሉ እየተረጋገጠ መምጣቱና ዜጎች ያለ ምንም ሥጋት የቀደመ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸውን በነፃነት መምራት የቻሉበት ብሩህ ድባብ መፈጠሩ ተገለጸ።
የባለአደራ አስተዳደሩ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች በመድረስ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ተቋማትም በሙሉ አቅማቸው ወደ ሙሉ አገልግሎት እንዲገቡ የማድረግ ሥራውን በስኬት በማከናወን ላይ ይገኛል።
የባለአደራ አመራር አደራጅ ቡድን አስተባባሪው ብርሃነ ገብረፃዲቅ እንደገለጹት፤ ኅብረተሰቡ አሁን ያገኘውን ሰላምና ነፃነት ለማስጠበቅና ላለማጣት ከለውጡ አመራርና ከመንግሥት ጋር በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ንቃት እየሰራ ይገኛል።
የሕዝቡን ቀጥተኛና ነፃ ምርጫ መሠረት በማድረግ እየተከናወነ ባለው የባለአደራ አመራሩን እስከ ታችኛው መዋቅር የማደራጀት ሂደትም በሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ምክንያት አሁን ላይ 60 በመቶ መጠናቀቁን አስተባባሪው አረጋግጠዋል።
የባለአደራ አስተዳደሩ መዋቅር እየተሟላ በሄደ ቁጥር የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ማስገባት የተቻለ ሲሆን ባንኮች፣ የንግድ ተቋማትና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አሁን ላይ በሙሉ አቅማቸው ተነቃቅተው ወደ አገልግሎት ገብተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በባለአደራ አስተዳደሩ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪው ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ለመንግሥት ሠራተኛው የደመወዝ ክፍያ እንዲጀምር በተደረገው ጥረት መሠረት ከዛሬ ጀምሮ ደመወዝ መክፈል ይጀመራል ብለዋል።
የባለአደራ አስተዳደሩ የትግራይ ክልል ሕዝብ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ያሳየውን ሁለንተናዊ ድጋፍና ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።