ቀጥታ፡

በዞኑ ለበጋ መስኖና ለመጪው መኸር የሚውል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል

ባህር ዳር፣ ጥቅምት 24/2019(ኢዜአ)፡-በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለበጋ መስኖና ለመጪው መኸር ሰብል ልማት የሚውል ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ነጋ መከተ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለበጋ መስኖና ለመጪው መኸር ሰብል ልማት 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ስራው እየተከናወነ ይገኛል።

በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ ከ155 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ እስካሁን በተደረገ ጥረት የዕቅዱን 75 በመቶ ማሳካት እንደተቻለም ገልጸዋል።

ከመደበኛ ኮምፖስት በተጨማሪ ከ10 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የባዮጋዝ ተረፈ ምርትና ከ14 ሺህ 800 ኩንታል በላይ ቨርሚ ኮምፖስት ተዘጋጅተው አሁን ላይ ለመስኖ ልማት ስራው ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን አመልክተዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ንጥረ ነገር ይዘት እንዲሻሻልና ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ፣ አርሶ አደሩ ለፋብሪካ ማዳበሪያ ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ እየቀነሰ እንዲመጣ አስችሏል።

የአርሶ አደሩ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ጠቀሜታና ዝግጅት ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ፣ በአካባቢው በቀላሉ ከሚገኙ አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠሎችና ከተረፈ ምርት ጥራቱን የጠበቀ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ እየተጠቀመ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዞኑ የጓንጓ ወረዳ አርሶ አደር መኮንን ፈንታው እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት የጥራት ደረጃውን ጠብቀው ባዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአንድ ሄክታር መሬት የበቆሎ ሰብል በማልማት ጥሩ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮም አንድ ሄክታር የእርሻ መሬታቸውን በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማልማት አቅደው ወደ ስራ በመግባት እስካሁን 20 ኩንታል ማዘጋጀት እንደቻሉ አመልክተዋል።

ባለሙያ በሚሰጣቸው ሙያዊ ምክረ ሃሳብ ታግዘው የተፈጥሮ ማዳበሪያን አዘጋጅተው መጠቀም ከጀመሩ ዓመታትን እንዳስቆጠሩ የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር አልጋነህ አካል ናቸው።

በዚህ ዓመትም ከ30 ኩንታል በላይ ለማዘጋጀት አቅደው እስካሁን 10 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት እንደቻሉ ገልጸው፣ በቀጣይ ዕቅዳቸውን በማሳካት ለፋብሪካ ማዳበሪያ መግዣ ሊያወጡ የሚችሉትን ወጪ ለማስቀረት እየሰሩ መሆኑን ገለጸዋል።

በዞኑ በበጋ መስኖና በመጪው መኸር ሰብል ልማት ከ165 ሺህ 700 በላይ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተጠቅሞ ለማልማት የተቀመጠው ግብ እንዲሳካ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም