ቀጥታ፡

እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን!

አንዳንድ ቀናት አሉ፤ ትውልድ በእምባ የሚያስታውሳቸው፣ ለዘላለም እንዳይደገሙ የሚመኛቸው፣ ከታሪክ በመማር የወደፊት ስህተቶችን ለመከላከል እንደ ትምህርት የሚወስዳቸው። እነኝህ ቀናት በትውልድ ልብ ውስጥ የሚቀሩ በታሪክ ተከትበው ዘመን የሚሻገሩ ናቸው።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በዚህ ዕለት ለዓመታት ሕዝባቸውን ሲጠብቁ የኖሩ ጀግኖች በሚያምኑት ወገን ክዳት ተፈጽሞባቸዋል። ለሀገርና ለሕዝብ ክብር የቆሙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከፊት ይጠብቁት በነበረው ጠላት ሳይሆን ከኋላቸው በመጣ ወገን ክህደት ተመትተዋል። ሀገሬንና ሕዝቤን ብለው የተሰለፉ ወታደሮች በእጅጉ አሳዛኝ የሆነ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል።

የሕዝብ ሰላም እንዲጠበቅ፣ ዜጎች በነፃነት ወጥተው እንዲገቡና ሀገር በሰላም እንድትኖር የራሳቸውን ሕይወት ሳይሰስቱ ለአደጋ የሚያጋልጡ ጀግኖች ናቸው። በዱር በገደሉ ኑሯቸውን አድርገው የሀገር ዘብ የሆኑ፣ ታሪክን ያስጠበቁና ሉዓላዊነትን ከጥቃት የተከላከሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የጀግንነት ተምሳሌቶች ናቸው።

እነዚህን ጀግኖች ያሰባሰባቸው የሀገር ፍቅር፣ አንድ ያደረጋቸው የሠንደቅ ዓላማ ክብርና ለኢትዮጵያ የገቡት ቃለ መሐላ ነው። በአንዲት ሀገር ያምኑ፣ በኢትዮጵያዊነት የጋራ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ወታደሮች በዚያ ዕለት ከባድ ክህደት ደረሰባቸው።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን ልብ የሚሰብር ዜና የሰሙበት፣ እናቶች የልጆቻቸውን አሳዛኝ ሞት እያሰቡ በሐዘን ያነቡበትና ሀገር የተከዘችበት ዕለት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

ይሁን እንጂ የተከዱት ጀግኖች በሐዘንና በተስፋ መቁረጥ አልተሸነፉም። ለሀገራቸው በገቡት ቃል ኪዳንና በሉዓላዊነቷ ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት ተመስርተው ተነስተዋል። ክህደትና መከራ ቢደርስባቸውም የሀገር ግዴታቸውን አልተዉም፤ ጽናታቸውን አስመስክረው በወታደራዊ ብቃትና በጀግንነት ታሪክ ሠርተዋል።

ጥቅምት 24ን የምናስታውሰው ክህደትን ለመወገዝ፣ የሠራዊቱን መሥዋዕትነት ለማክበር፣ የሕዝብና የሠራዊትን ትስስር ለማጠናከርና ታሪክ ዳግም እንዳይደገም ለመማር ነው። እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን!

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም