ቀጥታ፡

የካፒታል ገበያ፡ የነገዋ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የነገዋን ሀገር የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚቀይር እና ለአዲስ ዕድገት መሠረት የሚጥል መዋቅራዊ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።

የካፒታል ገበያ ሥርዓት በአዲስ መልክ መመለሱ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊና ግልጽ የፋይናንስ አማራጭ የሚያሸጋግር ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

ይህ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ወደ ምርታማ ኢንቨስትመንት ለመቀየር፣ የንግድ ድርጅቶችን አቅም ለማሳደግ እና የሀገሪቱን የብድርና የዕዳ ጫና በዘላቂነት ለማቃለል ታስቦ የተዘረጋ የነገ መደላደል ነው።

ዘመናዊ የካፒታል ገበያ በሕጋዊ መንገድ የተጀመረው የካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲጸድቅ ነው።

አዋጁን ተከትሎ ገበያውን በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን (ECMA) የተቋቋመ ሲሆን፣ ግብይቱን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (ESX) ደግሞ በመንግሥትና በግል አጋርነት (PPP) ተመሠረተ።

ይህ የዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያን (ESX) በሳይንስ ሙዚየም በይፋ መርቀው ያስጀመሩ ሲሆን፣ መደበኛ የቀጥታ የንግድ ግብይት (Live Trading) ደግሞ በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም. ላይ በይፋ ተጀምሯል።

የካፒታል ገበያው የነገን ብሩህ ተስፋ በሚያሳይ መልኩ ከጅምሩ በርካታ ግዙፍ ተቋማትን ማሳተፍ ችሏል። የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ በዲጂታል መንገድና በቴሌብር ጭምር በመታገዝ ከ47 ሺህ በላይ አዳዲስ ዜጎችን በማሳተፍ የመጀመሪያው በይፋ የተመዘገበ ኩባንያ በመሆን ታሪክ ሠርቷል።

ይህንን ተከትሎ በርካታ የግል የፋይናንስ ተቋማትና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አክሲዮኖቻቸውን በገበያው ላይ በይፋ ማስመዝገብ የጀመሩ ሲሆን፣ ይህም ለገበያው መነቃቃት ትልቅ መሠረት ጥሏል።

በተጨማሪም የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ አገበያዮችና ደላላ ኩባንያዎች የሥራ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፣ በባንኮች የእርስ በርስ የአጭር ጊዜ የገንዘብ መበዳደሪያ ገበያ ላይ የተመዘገበው አጠቃላይ የግብይት መጠን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ማለፉ የነገውን የገበያ አቅምና አስተማማኝነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

የዚህ ግዙፍ የፋይናንስ መድረክ ዋና ዓላማና ለነገዋ ኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ ሀገሪቱን በባንክ ብድር ላይ ብቻ ከምትመሰረተው የፋይናንስ ጥገኝነት ማላቀቅና አማራጭ የረጅም ጊዜ የካፒታል ምንጭ መፍጠር ነው።

ኩባንያዎችና መንግሥት አክሲዮንና ቦንድ በመሸጥ ለትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የሚሆን ገንዘብ በቀጥታ ከሕዝብ መሰብሰብ እንዲችሉ ያደርጋል።

ይህ አሠራር የመደመር መንግሥት ገንዘብ በማተም ወይም ከብሔራዊ ባንክ በመበደር የሚፈጥረውን የዋጋ ግሽበት በእጅጉ የሚቀንስ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡም ገንዘቡን በባንክ ቁጠባ ብቻ ከማስቀመጥ ባለፈ በትላልቅ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት አድርጎ የትርፍ ተካፋይ እንዲሆንና በነገዋ ኢትዮጵያ የሀብት ፍትሐዊ ክፍፍል እንዲሰፍን ያደርጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገበያውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ ይህ ገበያ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የፋይናንስ ነፃነት የሚያረጋግጥ መሣሪያ ነው።

የካፒታል ገበያው ማንኛውም ዜጋ በቀላሉ የትላልቅ ባንኮችና ተቋማት ባለቤት የሚሆንበት የነገ መድረክ ነው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ማዛወር ዓላማው ተቋማቱ ዓለም አቀፍ አሠራርን፣ ግልጽነትንና ዘመናዊ ተጠያቂነትን እንዲላበሱ ለማድረግ ሲሆን፣ የግል ዘርፉ የነገዋ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሞተር እንዲሆን መንግሥት ሙሉ ዋስትናና ከለላ ይሰጣል።

የካፒታል ገበያው ውጤታማነት በዋናነት የተመሠረተው ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያና የመረጃ ሥርዓቶችን በመተግበር ላይ ሲሆን፣ የኢትዮ ቴሌኮም የመጀመሪያ ዙር አክሲዮን በቴሌብር መጠናቀቁ ለነገው ዲጂታል መሠረተ ልማት ትልቅ ማሳያ ነው።

ገበያው ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የማኅበረሰቡን የፋይናንስ ግንዛቤ ማሳደግ፣ የኩባንያዎችን የሒሳብ አያያዝ ግልጽነት ማረጋገጥ እና ያልተገባ የገበያ ማጭበርበርን መቆጣጠር የመሳሰሉ የቤት ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።

ወደፊት ገበያውን ይበልጥ ለማስፋፋት የተቀመጡት ቀጣይ ስትራቴጂካዊ ትከረቶች ገበያውን ቀጣናዊና ዲጂታል ማድረግ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም