ዓለም አቀፋዊ የሰላም አምባሳደርነት: የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰላም ማስከበር ልዕልና - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፋዊ የሰላም አምባሳደርነት: የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰላም ማስከበር ልዕልና
የመከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበርን ከማስከበር ባሻገር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በዓለም አቀፍ መድረክ የሰላም ዋስትና ሆኖ በማገልገል የጎላ ታሪክ ባለቤት ነው።
ሠራዊቱ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ሀገራት ሁሉ የላቀ ስነ-ምግባርና ፍጹም የሰብዓዊነት እሴት በማሳየት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ከበሬታን በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ አትርፏል። ይህ ዓይነቱ የጀግንነት ታሪክ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ ያላትን ተሰሚነት እና ክብር በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አድርጎታል።
የሀገሪቱ የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ታሪካዊ መነሻ የሚጀምረው እ.እአ. በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኮሪያ ልሳነ ምድር በተሰማራበት የሰላም ማስከበር ተልእኮ ሲሆን፣ የሠራዊቱ አባላት በነበራቸው የማይናወጥ ፅናት እና አስደናቂ የወታደራዊ ጥበብ ዓለምን ያስደመሙበት ወቅት ነበር።
በወቅቱ የነበረው የሰላም ማስከበር ስራ የሰራዊቱን ከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የሚያሳይ ታሪክ ሆኖ አልፏል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ እ.አ.አ በ1960 የኮንጎ ሪፐብሊክ ከነፃነት ማግስት የገጠማትን የሀገር ውስጥ ቀውስ ለመፍታት የተመደቡ የመጀመሪያዎቹ የሰላም አስከባሪዎች በመሆን የተሰጣቸውን ከባድ ተልእኮ በላቀ ድል አጠናቀዋል።
ከዚያም ባለፈ ሰራዊቱ በሩዋንዳ የተከሰተውን አስከፊ ሰብዓዊ እልቂት ለመግታት በመሃል በመግባት የበርካታ ንጹኃንን ሕይወት መታደግ የቻለ የሰብዓዊነት አርአያ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአሁኑ ወቅትም ቢሆን በአፍሪካ ውስጥ ለሚታዩ ግጭቶች ፍጹም እውነተኛ የሰላም አለኝታ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በደቡብ ሱዳን በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ግዳጆች ላይ ገለልተኛ፣ እውነተኛና ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በማረጋገጥ የተሰጠውን ዓለም አቀፍ ተልእኮ በብቃት እያከናወነ ይገኛል።
በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ውስጥ ቀጣናዊ ስጋት የሆነውን አሸባሪ ቡድን በመዋጋትና የመንግሥትን መዋቅር ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የከፈለው መስዋዕትነት በታሪክ መዝገብ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው።
ሠራዊቱ በቁልፍ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ላይ ሰላምን በማስከበር የአካባቢው ማኅበረሰብ በተረጋጋ ሁኔታ ኑሮውን እንዲኖር አስችሏል።
ሠራዊቱ የቀጣናውን ተለዋዋጭ የደኅንነት ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰጠውን ተልዕኮ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተወጣ ሲሆን፣ አህጉራዊ ችግሮችን በሀገር በቀል አቅምና መፍትሔዎች ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በተግባር ማረጋገጡን ቀጥሏል።